በጎፋ ዞን በቀጣይ 6 ወራት የሚተገበር የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ዕቅድ ዙሪያ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል

በጎፋ ዞን በቀጣይ 6 ወራት የሚተገበር የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ዕቅድ ዙሪያ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል

በዞኑ የተመረጡ ሁለት ተራሮችን ለማልማትም ከየመዋቅሩ አመራሮች ጋር የርክብክብ ስነ-ስርዓት በመድረኩ ተከናውኗል።

የጎፋ ዞን ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦረና ቦላዶ የአካባቢ ብክለት በሰዎች፤ በእንስሳትና አጠቃለይ ህይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚያደርሰውን አካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳት በመቀነስና በመከላከል ንፁህ፣ ጤናማና ምቹ አካባቢያዊ ሁኔታ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረግ ዘመቻ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ብክለትን የመከላከል የንቅናቄ ዘመቻ ለለሚቀጥሉት 6 ወራት የሚቆይ ሲሆን በዚህ ወር ይፋ የምናደርገው የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል መሆኑን ተናግረዋል።

በምንተነፍሰው አየር ላይ የፕላስቲክ ብክለት ጫና ከፍተኛ ነው ያሉት ኃላፊው በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ዓለማችን 1.3 ቢሊየን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻ ለመሸከም ትገደዳለች ሲሉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው አብራርተዋል።

ንቅናቄው ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ ሲሆን በህግ የተቀመጡ ድንጋጌዎችንም ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ዜጎች ባልተበከለና አካባቢያዊ ንጽሕናው በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብትን የሚጋፋ ተግባራትን ከመከላከልና መቆጣጠር አኳያ ያለን ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ የችግሩን ግዝፈት አጉልቶታል ብለዋል።

ለዚህም የብክለት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ከማስወገድ አኳያ የነቃ ተሳትፎ ማድረግና በዕቅድ የተመላከተ ተግባር ሊከናወን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

አክለውም በዓለም ላይ እየተከሰተ የሚገኘው የተፈጥሮ አደጋዎች መነሻ የአየር ብክለት ውጤት በመሆኑ የሰው ልጅ ከቸልተኝነት ወጥቶ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው የተዘጋጀው እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በዞኑ የተመረጡ ሁለት ተራሮችን ለማልማት ከየመዋቅሩ አመራሮች ጋር የርክብክብ ስነ-ስርዓት በመድረኩ ተከናውኗል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን