በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቴክኖሎጂ በማሸጋገርና በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጣለባቸው ኃላፊነት የጎላ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ ኢንቨስትመንት ስራ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከራሳቸው አልፎ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገርና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የተጣላባቸው ኃላፊነት የጎላ መሆኑ ተመላክቷል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጎምቦራ ወረዳ እየተሰሩ የሚገኙ የተለያዩ ኢንቨስትመንት ስራዎች ጉብኝት አድርገዋል::
በጉብኝት ወቅት የተገኙት በሀድያ ዞን የጎምቦራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ጎበና፥ የፋብሪካው ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው፥ ግንባታቸው ሲጠናቀቁ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል::
ባለሀብቶች ለልማት የወሰዱትን መሬት አልምተው ማህበረሰቡን በተገቢ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ አብርሃም አክለዋል::
የፋብሪካ ስራ እንቅስቃሴ አበረታች በመሆኑ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበትና የአካባቢ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስተዳዳሪ አመላክተዋል::
ንጋት የታሸገ ንጹሕ የተፈጥሮ መጠጥ ውሃ የተሠማሩ የአክሲዮን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ ለምቤ፥ ከ62 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግቦ ፍቃድ ወስዶ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ፋብሪካው በ2017 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ስራ እንደሚጀምር ገልጸው ለ55 ቋሚና ከ200 ለሚበልጡ ወገኖች ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል::
ከፋብሪካ ግንባታ ጎን ለጎን የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተሻሻለ የቡና ችግኝ እና የጓሮ አትክልቶችን እያለሙ እያሰራጩ መሆናቸውን ገልጸዋል::
የሀድያ ዞን ኢንቨስትመንት እና ኢንዲስትሪ መምሪያ የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ ወ/ሪት አሰገደች ዘውዴ እንደገለጹት፥ በዞኑ 353 ፕሮጀክቶች በሆቴልና ቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ ልማት እና በእርሻ ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው መሬት በማልማት ከራሳቸው አልፎ ለአከባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በገጠር ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች ከራሳቸው አልፎ ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂ ለማሸጋገርና በአካባቢው መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ውል በመግባት ፈቃድ እንደሚወስዱ የገለጹት ቡድን መሪዋ፥ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠርም ሌላኛው ተግባር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ መሬት ወስደው ሳያለሙ የቆዩ መኖራቸው ገልጸው፥ 15 ባለሀብቶች በተገቢው ባለማልማታቸው የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሥጠታቸውን አክለዋል።
የንጋት የተሻጋ ንጹሕ የተፈጥሮ የመጠጥ ውሃ የአክሲዮን ማህበር አባል አቶ ግርማ ሽታ በበኩላቸው በተለይ አካባቢው ለቡናና ለፍራፍሬ ምርቶች ምቹ በመሆኑ ከፋብሪካ የሚወጣውን ውሃ በተገቢው በመጠቀም ማበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል::
በ62 ሚሊዮን ብር የተቋቋመ አክሲዮን ማህበሩ ዛሬ ላይ ወደ 96 ሚሊዮን ማደጉንም አቶ ግርማ ጠቅሰዋል::
አንዳንድ ያነጋገርናቸው ዜጎች እንደተናገሩት በፋብሪካው በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በዚህም እራሳቸውን ችለው ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቃቸው ተጠቃሚዎቹ አመላክተዋል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ