የበልግ እርሻ ሰብል እንክብካቤን በተገቢው እያከናወኑ መሆናቸውን አንዳንድ በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

የበልግ እርሻ ሰብል እንክብካቤን በተገቢው እያከናወኑ መሆናቸውን አንዳንድ በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የበልግ እርሻ ሰብል እንክብካቤን በተገቢው እያከናወኑ መሆናቸውን አንዳንድ በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በሰብል እንክብካቤና የአረም ቁጥጥር ማነስ ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰት አስፈላጊው ግብዓት በወቅቱ እንዲደርስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

በመስክ ምልከታ ወቅት ካነጋገርናቸው የዳሞት ወይዴ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር መላኩ ጎኣ፣ ወልደ ጃርሳ እና በርገነ ባሳ እንደገለጹት፤ በበልግ እርሻ ወቅት ከቡቃያ ጀምሮ ለለማው ሰብል ተገቢ ክብካቤና የአረም ቁጥጥር ሥራ በማከናወን ምርታማነትን ለማሳደግ እየተጉ ነው።

የግብርና ግብአት ዩሪያ በመጠቀም የአረም ቁጥጥር፣ ኩትኳቶና መሰል የእንክብካቤ ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸው የሚነሱት አርሶአደሮች ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

አርሶ አደሮች ወቅቱን በጠበቀ ሁኔታ ሰብልን መንከባከብና የአረም ቁጥጥር ማድረግ እንዲችሉ ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት በዳሞት ወይዴ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊና እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ቡጌ ናቸው፡፡

በተያዘው የበልግ እርሻ 7ሺህ 1መቶ አርባ አምስት ሄክታር በዘር የተሸፈነ እንደሆነ የሚናገሩት ም/ኃላፊው አርሶ አደሮች የሰብል እንክብካቤና አረም-ቁጥጥር በወቅቱ ማከናወን እንዲችሉ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር ሁኔታው ምቹና ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ በመዝነቡ 783ሺህ 1መቶ 61 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።

የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቸርነት ኤፌሶን በሰብል እንክብካቤ እጥረት ምክንያት የምርት መቀነስ እንዳይከሰት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርሱ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በወረዳው በልግ እርሻ በቆሎ በብዛት እንደሚመረት ገልጸው፣ አሁን እየለማ ካለው አጠቃላይ ማሳም 60 በመቶ የሚሆነው በቆሎ ሲሆን የቀረው በአዝዕርት ስብል መሸፈኑን ተናግረዋል።

በወረዳው ደጋማ ቀበሌያቸው የድንችና እንሰት ተክሎችን በስፋት በመትከል ድርቅ ለመቋቋም አስቻይ ሥራዎች በወረዳው እየተሰሩ መሆናቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ የክረምት ወራት የቡና ችግኝ በማባዛት ለአርሶአደሮች ለማቅረብ ወደ ተግባር እንደተገባ አስረድተዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች የዕለት ተዕለት የማሳ ክትትል ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቸርነት ከአምና 20 ከመቶ የተሻለ ምርት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የበልግ ምርት እጥረትን፣ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እና የምርት ዋጋ መጨመርን ታሳቢ በማድረግ በምርት ዘመኑ የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ መላው አርሶ አደሮች የሰብል እንክብካቤያቸውን አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

ዘጋቢ: ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን