እንደ ሀገር በትምህርት ጥራትና ውጤታማነት ላይ ያጋጠመውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት የጦራ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ገለፀ
በትምህርት ዝግጅቱ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ ሀገር ተረካቢ ዜጋ የማፍራት ብሩህ ራዕይ በሰነቀው የወራቤ ዩኒቨረስቲ መምህርና በጎ ፈቃደኛ ሳዲቅ ሽፋ በስልጤ ዞን ማዕከል ወራቤ ከተማ ዱና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጀመረው የበጎ ፈቃደኛ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት አሁን ላይ ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ በሁሉም አካባቢ ሰፋ ባለ መልኩ እየተሰጠ ይገኛል።
በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲከታተሉ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ተማሪዎች ትምህርቱ ለመደበኛ ትምህርታቸው አጋዥ እንደመሆኑ ያለማንም ቀስቃሽ በንቃት በመከታተል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በወራቤ ዩኒቨርስቲ በጎ ፈቃደኛ መምህራን እየተሰጠ ያለው ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት ያላቸውን ዕውቀትና ግንዛቤ ይበልጥ ከፍ ያደረገ በመሆኑ በትምህርት ውጤታማነታቸው የተሻለ ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረጉንም አስተያየት ሰጪ ተማሪዎች አመላክተዋል።
በጦራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእረፍት ቀን የበጎ ፈቃድ ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ እያለ ያገኘነው መምህር ሳዲቅ ሽፋ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህር ሲሆን ያለምንም ክፍያ በቅን ልቦና የሚከወነውን የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ከጀመረ ቆየት ማለቱን በመጠቆም አሁን ላይ በዘርፉ የተሳታፊ በጎ ፈቃደኛ መምህራንና የተማሪዎች የመማር ተሳትፎ ከፍ ማለቱን ተናግሯል።
በበጎ ፈቃድ የሚሰጠው ትምህርት እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ጥራትና ውጤታማነት ስብራትን በዘላቂነት ለማሻሻል መሰረት የሚጥል እንደመሆኑ በቀጣይም ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም መምህር ሳዲቅ ጠቁሟል።
ትውልዱን ከትምህርት ውድቀት መታደግ አላማ ያደረገው የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በተለይም በእንግሊዝኛና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ያደረገ እንደ መሆኑ ተማሪዎችን ለክልልና ብሔራዊ ፈተና ምዘናዎች ዝግጅት በመልካም ስነምግባርና ስነልቦና በብቃት እንዲዘጋጁ በማድረግ ረገድም አበርክቶው ጉልህ ስለመሆኑ በጎ ፈቃደኛ መምህሩ አስረድቷል።
ተግባሩ ጥራት ያለው ውጤታማ የመማር ማስተማር ተግባር ይጠናከር ዘንድ ጉልህ እገዛ ስላለው ለወራቤ ዩኒቨርስቲ በጎ ፈቃደኛ መምህራንና አጋር አካላት ከግብአት አቅርቦት ጀምሮ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የጦራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ካሚል ሙዘይን ገልጸዋል።
እንደሀገር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በመንግሥት በኩል ሰፊ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ መሆኑን በማስታወስ በዩኒቨረስቲ በጎ ፈቃደኛ ቅን መምህራን አማካኝነት እየተሰጠ ባለው የተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ጥሩ ለውጥ በመታየቱ የተሳታፊ ተማሪዎች ጥቁር ከፍ ማለቱን የገለፁት ደግሞ የጦራ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸይቾ ኑሪ ናቸው።
የበጎ ፈቃደኛ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርቱ የትምህርት ስብራቱን በተገቢው ለማከም ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን የጦራ ከተማ ከንቲባ አቶ ሁሴን ሱናሞ ተናግረዋል።
የማጠናከሪያ ትምህርቱ ተማሪዎችን በዕውቀትና ስነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል እንደመሆኑ ለዘርፉ መጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ከንቲባው አመላክተዋል።
በትምህርት ዘርፉ የሚጠበቀውን ጥራትና ውጤታማነት በተገቢው ለማረጋገጥ ከትምህርት ባለድርሻ አካላት በተጨማሪ ከበጎ ፈቃደኞችና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም በመጠቆም።
የማጠናከሪያ ትምህርቱ በቀጣይም ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተግባሩን ሁሉም ማገዝ እንዳለበት የገለፁት ከንቲባው በበጎ ፈቃድ የማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎችን በማገዝ ረገድ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በተገቢው በመወጣት ላይ የሚገኙ መምህራንን አመስግነዋል።
ዘጋቢ: አብዱልሃሚድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ