የመብራት መቆራረጥና መጥፋት በኑሮአቸዉ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ባዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ ዋካ ከተማ በተለያዩ ስራ ዘርፎች የተሰማሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ተናገሩ

የመብራት መቆራረጥና መጥፋት በኑሮአቸዉ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ባዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ ዋካ ከተማ በተለያዩ ስራ ዘርፎች የተሰማሩ ማህበረሰብ ክፍሎች ተናገሩ

በወረዳዉ መብራት ከጠፋ ከ10 ቀናት በላይ መቆጠሩም ተጠቁሟል፡፡

ወጣት ሙሉቀን ኃይሌና አስራት መንገሻ የየዕለት ኑሯቸዉን የሚመሩት ከእህል ወፍጮና ከቤትና ቢሮ ዕቃ ማምረት ከሚያገኙት ገቢ ነዉ፡፡ በዚህ ስራቸዉ ከራሳቸዉ አልፈዉ ለሌላ ሰዉ የስራ እድል መፍጠር የቻሉ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የመብራት መቆራረጥና መጥፋት በስራቸዉ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚሀም የቁጠባ ባህል ለማዳበር የገቡትን ዕቁብ መክፈል ከማቆማቸዉም በላይ ደንበኞቻቸዉ እየሸሹባቸዉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የከተማዉ ነዋሪዎች በከተማዉ እየተስተዋለ ያለዉ የመብራት መቆራረጥ በስራቸዉ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱን ነዉ የተናገሩት፡፡ በዚህም ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ብለን ተስፋ ብናደርግም እየተባባሰ ነው የመጣው ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸዉ አካላት ለችግሩ እልባት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

የወረዳዉ ምክትል አስተዳዳሪና ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኦርሳና ኦልታዬ ለመብራት መቆራረጥና መጥፋት ምላሽ ለመስጠት ጥረት ቢደረግም እልባት ሊያገኝ አልቻለም ነዉ ያሉት፡፡ ቢሆንም በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር አየተነጋገርን ነዉ ብለዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና የመሰረት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ በበኩላቸዉ በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ከመብራት መቆራረጥ ጋር ታያይዞ የሚነሳዉን ችግር ለመቅረፍ እየሰራን እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለችግሩ አንደኛዉ መንስኤ በተለያዩ ቦታዎች ከዋናዉ መስመር ጋር የዛፍ መገናኘት ነዉ ብለው ሌላዉ ደግሞ በዞኑ በርካታ ቦታዎች በአንድ መስመር ስለተገናኙ በአንድ ቦታ የተከሰተ ችግር ለሌላ ቦታም ችግር እየፈጠረ ማስቸገሩን ነዉ አቶ ተስፋዬ ያነሱት፡፡

በቀጣይ የመብራት መቆራረጥና መጥፋትን ለማስቀረት የዞኑ መንግስት ከክልልና ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እሸቱ ወርቅነህ – ከዋካ ጣቢያችን