ምክር ቤቶች ህብረተሰቡ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
በኮንሶ ዞን የኮልሜ ወረዳ ሽግግር ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የወረዳው ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ካፒኖ ኮርቶሎ መንግሥት የወረዳው ህብረተሰብ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኝ በ14 ቀበሌያትና 3 ማዘጋጃ ቤቶች በአዲስ መልክ ባደራጀበት፤ በቀበሌያት ልክ የወረዳው አባላት ቁጥር ለማሳደግ ከቀበሌያት ም/ቤት በሞሽን ወደ ወረዳ እንዲቀላቀሉ በተደረገበት፤ በአጎራባች አካባቢዎች መካከል ህዝባዊ ትስስሮች በተፈጠሩበት መካሔዱ ጉባኤውን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የ2016 ዓ.ም የአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች፣ የምክር ቤትና የፍርድ ቤት አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበዋል።
በቀረቡ የአፈፃፀም ሪፖርቶች ላይ ከምክር ቤቱ አባላት በርካታ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን የወረዳና የቀበሌያት ምክር ቤቶች አዳራሽ ግንባታ ተደራሽነትና የቀበሌያት ምክር ቤቶች ጉባኤዎችን በተገቢው መንገድ ማድረግና በህዝብ ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎችን ማድመጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።
በጤናው ዘርፍ የመድኃኒት አቅርቦትና አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶች፣ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በግብርናው ዘርፍ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት፣ በጅምር የቀሩ ግንባታዎች ማስቀጠል፣ በትምህርት ዘርፍ የግብዓት አቅርቦ ውስንነት፣ ገቢ አሰባሰብ አናሳ መሆን፣ ገቢ አመንጪ ተቋማትን ማጠናከር፣ ሠራተኞች በጊዜ በሥራ ላይ ተገኝተው ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ ህገ ወጥ የማዳበሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃዎችን ማጣራት፣ ምርጥ ዘር በጊዜ ያለማቅረብ ችግሮችን የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።
በፍትህ ዘርፍ ከፖሊስ፣ አቃቤ ህግ፣ ከሰላምና ፀጥታ ጋር በቅንጅት መሥራት፣ ሴቶች የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ በትኩረት መሥራት፣ በህግ መስመር መፈታት ያለባቸውና በዕርቅ መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማስተናገድ እንዲሁም የንቃተ ህግ ግንዛቤዎችን መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።
በፍርድ ቤት የሰው ሀይል ውስንነትና የግብዓት ችግር ቢስተዋልም የተመዘገበው አፈፃፀም አመርቂ እንደሆነም ተመላክቷል።
ከምክር ቤት አባላት በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርንግላንድ ላቀው እና የወረዳው ዋና አፈ ጉባኤ እንዲሁም የሥራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል የ2016 ግማሽ በጀት ዓመት የከተማና የገጠር መሬት የገቢ ምጣኔ ተመን እንዲሁም የተሻሻለው የ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ የበጀት አዋጅና መግለጫ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱ ተወያይቶበት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና የአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ሹመቶችም ቀርበው ጉባኤው መርምሮ አጽድቋል።
ዘጋቢ: አማሮ አርሳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ