የሳምንቱ እንግዳችን አቶ ደምመላሽ ንጉሴ ይባላሉ፡፡ የጨንቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ከባለሙያነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ከ10 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ በከተማው ስላለው እድገት፣ የመሰረተ ልማት ሥራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ
በገነት ደጉ
ንጋት፡- የጨንቻ ከተማ መቼ ተቆረቆረች? እድገቷስ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ደምመላሽ፡- ጨንቻ ዕድሜ ጠገብ ከተማ ናት፡፡ የድሮ አባቶች ከአዲስ አበባ ጋር እኩል እንደተቆረቆረች ነው የሚናገሩት።
በ1889 ዓ.ም አካባቢ እንደተቆረቆረች የታሪክ መዛግብትም ይናገራሉ። ከ1924 እስከ 1955 ዓ.ም ድረስ ለ12 ዓመታት ያህል የጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት መቀመጫ በመሆን ቆይታለች፡፡
በ1955 ዓ.ም የጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት መቀመጫ አርባምንጭ እስኪሆን ድረስ ጨንቻ በዋና ከተማነት ስታገለግል ቆይታለች። በኋላም እስከ 1983 ዓ.ም ደርግ ከስልጣን እስኪወርድ ድረስ የጋሞ አውራጃ መቀመጫ በመሆን አገልግላለች።
ከ1983 እስከ 2010 ዓ.ም ጥር ወር ድረስ ደግሞ 50 ቀበሌያት ያሉት የወረዳ ከተማ ወይም መቀመጫ በመሆን ያገለገለች ስትሆን አሁን ላይ የጨንቻ ከተማ አስተዳደር ሆናለች፡፡
ይህም በአጭሩ የ127 ዓመታት ታሪክ ያላት እድሜ ጠገብ ከተማ ያደርጋታል። ነገር ግን የእድሜዋን ያህል ለምታለች ማለት አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ ለምታለች ለሚለው እና የህዝብን ፍላጎት አሟልታለች ወይም በሚገባት ፍጥነት አድጋለች ብለን ስንጠይቅ መልሳችን አላደገችም ነው፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም ገና የለውጥ ጭላንጭል እያየች ያለች ከተማ ናት፡፡
ንጋት፡- በከተማዋ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ደምመላሽ፡- ከተማ አስተዳደር ከሆነች ጊዜ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለዓብነትም የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ መንገድ ሥራዎች፣ የዲች ግንባታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰርተዋል፡፡
ለዓመታት ተጓትቶ እና በተለያዩ አሰራር ችግር ውስጥ ቆይቶ የነበረው የሞርካ ዋጫ ግርጫ የመንገድ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ገደማ መድረሱን ተከትሎ በከተማዋ የለውጥ ጭላንጭል በግልፅ መታየት ጀምሯል። በዚህም ህዝቡ በጣም ተነቃቅቷል፤ ደስተኛም ነው፡፡
በከተማዋ አመራር በተቀያየረ ቁጥር ጥያቄው አዲስ በመሆን በርካታ ችግሮች ሲንፀባረቁ ነበር፡፡
ጉዳዩ ጥሬ እየሆነ በህዝቡ ዘንድ አጀንዳ እንዳይሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ በማስቀመጥ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በዚህም ከፌደራል፣ ከክልል፣ የዞን መንግስት እና የከተማ አስተዳደሩ በጋራ ፈንድ በማመቻቸት በ80 ሚሊየን ብር የጨንቻ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ ነው፡፡
ንጋት፡- ይህ ማለት ወጪውን በጋራ ይሸፍናሉ ነው? ዘርዘር ቢያደርጉት?
አቶ ደምመላሽ፡- የፌደራል መንግስት 50 በመቶ ወጪውን፣ 25 በመቶ የክልሉ መንግስት፣ የዞኑ መንግስት 12 ነጥብ 5 በመቶ እና 7 ነጥብ 5 በመቶ የከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም የከተማው ውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት 5 በመቶውን በመሸፈን ሥራው እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም የፊዚካል እና የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በተለይም የፊዚካል ሥራው የስራውን 23 በመቶ የሚሸፍን በመሆኑ እርሱን በማጠናቀቅ ሂደት ላይ ነን፡፡
እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት በርካታ ችግሮች በተቋራጭ በኩል ያሉ ሲሆን አሁን ላይ በዚህ ጊዜ ያልቃል የሚል ምላሽ ባይኖርም መልካም የሚባል ተስፋ አለው።
ንጋት፡- ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችስ እንዴት ይገለፃሉ?
አቶ ደምመላሽ፡- ከአስፓልት ስራ ጋር ተያይዞ የረጅም ዓመት የህዝብ ጥያቄ የሆነው የሞርካ፣ ዋጫ፣ ግርጫ እና ጨንቻ አስፓልት ስራ ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከሚሸፍነው 72 ኪሎ ሜትር በከተማው አስተዳደር 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በከተማው ውስጥ ስለሚያልፍ የከተማ አስተዳደሩ ተገቢ ድጋፍና ክትትል በማድረጉ ወደ ማጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ደርሷል፡፡
ለህዝብ ጥያቄም ምላሽ ለመስጠት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ አፈፃፀሙም ወደ 98 በመቶ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተጠናቋል፡፡
የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም ህዝብን በማሳተፍ ተጀምረዋል፡፡ በዚህም ህዝቡም በተከፈቱ አራት አካውንቶች ተሳትፎውን እያደረገ ነው፡፡
ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ያሉ የአካባቢው ተወላጆች ንቅናቄ ተፈጥሮ “ከእኔ ለጨንቻዬ ”በሚል በነቂስ እየተሳተፈ ነው፡፡ በቀጣይም ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ከመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በጥቅምት ወር በጨንቻ ከተማ የነበረው ትልቅ እና ግዙፍ ትራንስፎርመር ድንገት ተቃጥሏል፡፡
በዚህም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የሀይል መቆራረጥ አጋጥሟል፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት እስከ ክልል ድረስ ምላሸ ለማግኘት ሄደን 14 ቀን ባልሞላ ጊዜ ነው ወደ ዲታ ወረዳ ከሚሄደው መስመር መውሰድ የተቻለው፡፡
ነገር ግን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የተቃጠለው ትራንስፎርመር ተስተካክሎ እንዲመጣ ከዞኑ መንግስት ጋር እየተሰራ ነው።
ንጋት፡- ከተማዋ በአፕል እና በወተት ምርት እንደመታወቋ በመሆኗ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆናለች?
አቶ ደምመላሽ፡- አፕል መፍለቂያው ተብሎ የሚታወቀው ጦሎላ አካባቢ ነው። እዚህም አካባቢ የ73 ዓመት ቆይታ ያላት ፔር አፕል ወይም እናት አፕል ተብላ የምትታወቅ የአፕል ዛፍ አለች።
ያኔ በሰዓቱ እንደ አጥር የተቀመጠች ሲሆን ከሚሶኒያዊያን ጋር ቁርኝት ያላቸው ሰዎች ነበር ወደ ከተማዋ በስፋት በማባዛት ያስገቡት፡፡ ዛሬ ግን በሁሉም ህብረተሰብ ጓሮ አፕል እንደ አቅማቸው ያህል አይጠፋም፡፡
ለአፕል የደጋው አየር ይበልጥ ተስማሚ ሲሆን የደጋ ፍራፍሬ በመባል ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለአፕል ምርት ትልቁን ሚና የተጫወተው የጦሎላ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሲሆን በወቅቱ ከወርልድ ቪዥን ጋር በመተባበር በአርሶ አደሮች ጓሮ እና ሰፋፊ ማሳ ላይ ስልጠና በመስጠት በስፋት ጨንቻን በአፕል አስተዋውቀዋል እና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
በዚህም ማህበራት በአንድ አካባቢ በአርሶ አደሩ ማሳ የአፕል መንደር በማለት በስፋት ተሰርቷል፡፡ አርሶ አደሩም ሆነ የአካባቢው ህብረተሰብ ከችግኙም እና ከፍሬው ተጠቃሚ ናቸው፡፡
በአፕል ምርት ከሳር ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት ያልተሸጋገረ እና መኪና ያልገዛ ሰው ጥቂት ነው፡፡ የራሳቸውንም ይሁን የልጆቻቸውን ህይወት ቀይረዋል፡፡ ቅርስም አፍርተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አምና ላይ በርካታ ችግኞች ከዚሁ ሄደው ተተክለዋል፡፡ የገበያው ትስስርም ጥራቱን በማስጠበቅ ዙሪያ በትኩረት ተሰርቷል። ሆኖም ግን ገና ብዙ ይቀረናል። ሁሉም አርሶ አደር እና የከተማዋ ነዋሪ በሚፈለገው ልክ ተጠቅሟል ለሚለው ምላሽ ለመስጠት ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ከወተት ጋር ተያይዞ 28 ሺህ ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞች ያሉ ሲሆን በቀን ከ3 እስከ 40 ሊትር ወተት የሚሰጡ ናቸው። ዓምና ላይ በክልሉ በተደረገው ውድድር 40 ሊትር ወተት በመስጠት ያሸነፈችው ከብት በጨንቻ ከተማ ነው ያለችው። እርሷን ጨምሮ በርካታ ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞች በከተማዋ ስለሚገኙ በቀን ከ3ሺህ እስከ 4ሺህ ሊትር በመስጠት ወደ አርባምንጭ በሴቶችም ይሁን በወጣቶች ማህበር ይቀርባል፡፡
ላሞቹ በሶስት ዘዴ ዝርያቸው የሚሻሻል ሲሆን የመጀመሪያው በኮርማ ማዳቀል፣ መደበኛ ድቀላ እና በዓመት አንድ ጊዜ በዘመቻ ሲንክሮናይዜሽን ሥራዎች ይሰራሉ። በልዩነት የሴት ጥጃ የምትሰጥ ተብሎ በተለየ ሁኔታ እየተሰራ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ንጋት፡- የአካባቢው ሰላምና ፀጥታን የማስጠበቁ ስራስ?
አቶ ደምመላሽ፡- አካባቢው ሰላም ነው፡፡ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግሮች የሚንፀባረቁበት አይደለም፡፡ አብዛኛው የአካባቢው ተወላጆች ከቡራዩ እና ከሸገር ሲቲ የተፈናቀሉ ቢሆኑም በልማቱ በመሳተፍ እና በሽመናው ሥራ በመሰማራት አምርተው ለገበያ ከማቅረብ ባሻገር የራሳቸውን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመምራት ደፋ ቀና እያሉ ናቸው፡፡
ምንም ዓይነት ጎልተው የወጡ ችግሮች የሉም፡፡ እራስን ለማሻሻል ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የሚገለፁ ጉዳቶች አልተስተናገዱም፡፡
ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?
አቶ ደምመላሽ፡- ከሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ ይህንን ጋዜጣ የሚያነቡ ወገኖቻችን ሁሉ “ከእኔ ለጨንቻዬ በማለት የጀመርነውን የልማት ጉዞ በጋራ እና በመቀናጀት እናሳካ” የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ደምመላሽ፡- እኔም አመሰግናለሁ።.
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ