በኮሬ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ዩኒት የወጣቶች ፌደሬሽን በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማጠናከር ኮንፈረንስ ተካሄደ

በኮሬ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ዩኒት የወጣቶች ፌደሬሽን በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማጠናከር ኮንፈረንስ ተካሄደ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮሬ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ዩኒት የወጣቶች ፌደሬሽን በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማጠናከር ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኮሬ ዞን ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ የግብርና መምሪያና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስታረቀኝ አንደባ፣ ወጣቱ ህብረተሰብን ማሻገር በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ፣  በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ለራሱም ሆነ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ኃላፊነቱን አውቆ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ዩኒት ተወካይ አቶ ታምራት ታደለ፣ የወጣት አደረጃጀቶችን መልሶ ለማደራጀትና ለማጠናከር የተዘጋጀ ዞናዊ ማጠቃለያ ኮንፈረንሱን ሰነድ በአቀረቡበት ወቅት፣ ወጣት ፈጣንና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ፣ የተሟላ ሠላም ለማስፈንና ቀጣይነት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት እውን ለማድረግ ሚናው ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

በዞኑ በሚካሄደው የሠላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።

ዞናዊ የተማሪዎች ውጤትና ሥነ-ምግባር ስብራት ማሻሻያ ልዩ ንቅናቄ ዕቅድ ሰነድ ያቀረቡት የኮሬ ዞን ትምህርት መምሪያ የልማት ዕቅድ ባለሙያ አቶ ወንድወሰን ጥላሁን፣ በትምህርት ዘርፍ ከምዝገባ እስከ ልየታ የወጣቶች ተሳትፎ ህብረተሰብን ከማንቃት አንፃር ከፍተኛ በመሆኑ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ወጣቶችን ይዘን ችግሩን እንፈታለን ብለዋል።

የዲጂታል ሚዲያ ንቅናቄ ሰነድ ያቀረቡት የኮሬ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ሚዲያ ኃላፊ አቶ አባይነህ አየለ፤ ዲጂታል ሚዲያ አዎንታዊ ጥቅሞች እንዳለው በመግለጽ በአግባቡ ካልተጠቀሙ አሉታዊ ተጽእኖ መኖሩን በማወቅ ተጠቃሚዎ ሚዲያን በጥንቃቄ ለበጎ ዓላማ መጠቀም እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል መምህር አሳዬ አሸናፊ፣ መምህርት ነፃነት ገዛኸኝ፣ ወጣት ካሮት ካሳዬ እና ሌሎችም ከውይይቱ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸው በራስ ጉዳይ ዙሪያ በመወያየት በሁሉም ዘርፍ በመሳተፍ ለህብረተሰቡ መልካም አርአያ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል።

ለራሳችን ተለውጠን ህብረተሰብን መለወጥ ይጠበቅብናል ያሉት ተሳታፊዎቹ የተቀበሉትን ተልዕኮ ወደ ህብረተሰቡ በማድረስ በመልካም ስነምግባር እንደሚሠሩ በመግለጽ ከሚያገኙት የወር ገቢያቸው አቅም በፈቀደ መጠን ለዞኑ ተማሪዎች መጽሐፍ ግዥ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።

በኮሬ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ዩኒት የወጣቶች ፌደሬሽን በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ለማጠናከር የተዘጋጀው ኮንፈረንስ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና የወጣቶች ተወካዮች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን ሌሎችንም ተደራሽ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን