በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ የተቋራጮች አቅም ውስንነት ችግር አለ – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኢጀንሲ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ እየተሰሩ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ የተቋራጮች አቅም ውስንነት ችግር መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኢጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በክልሉ የሚገነቡ የተለያዩ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኢጀንሲ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ካሳዬ ተክሌ በክልሉ እየተሰሩ ያሉ 16 የመስኖ ፕሮጀክቶች አሉ ብለዋል።
ከዚህ በፊት በነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጭምር ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶች ነበሩ ያሉት ኃላፊው መጠናቀቅ በነበረባቸው ጊዜ ያልተጠናቁ እንዳሉና ለዚህ ደግሞ የተቋራጮች አቅም ውስንነት ምክንያት ነው ብለዋል።
ከተጀመሩት ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት አመት 7ቱን ለመጨረስ መታቀዱን የገለፁት ደግሞ የኤጀንሲው ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር መሀመድ ሲራጅ ናቸው።
በክልሉ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተቋራጭ ተቋማት አዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተቋቋመ በኋላ የክልሉ የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኢጀንሲ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ተቋራጮቹ ወቅታዊ የገበያ ሁኔታና የግብዓት አቅርቦት ችግር ስራዎቹ በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ የፕሮጀክት አፈፃፀም ክፍተት ያለባቸው እንደ የመጌቻ የመስኖ ፕሮጀክት ተቋራጭ የመሳሰሉት በቀጣይ እንዲስተካከሉ አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
በዚህ አመት እንዲጠናቀቁ የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ተቋራጮቹ ቃል ገብተዋል።
ዘጋቢ፡ በአሰፋ ፀጋዬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ