የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለፍትህ ዘርፍ ሪፎርም የሚሆን ግብዓት ማሰባሰቢያ ህዝባዊ መድረክ በሳውላ ማዕከል አካሄደ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በፍትህ ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጠቃላይ ሪፎርም ለማድረግ በማሰብ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ከጎፋ ዞን ምክር ቤት ጋር በመተባበር የግብዓት ማሰባሰቢያ ህዝባዊ የምክክር መድረክ በሳውላ ማዕከል አድርጓል።
የውይይቱን መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የደቡብ ኢትዮጽያ ክልል ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ የህግ ጉዳዮች አማካሪ ወ/ሮ መስከረም ወ/ማሪያም ግብዓት የማሰባሰቡ ሥራ በስድስቱ የክልሉ ማዕከል ከተሞች ላይ የሚካሄድ ሲሆን በሚቀጥሉት 3 አመታት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑም አመላክተዋል።
በሳውላ ማዕከል በተካሄደው ህዝባዊ መድረክ ላይ ከጎፋ ዞን ከሁሉም መዋቅሮች የተውጣጡ አካላት ተሳትፈው በፍትህና ህግ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።
በፍርድ ቤቶች በዳኝነት አሰጣጥ ሂደት የተራዘመ ቀጠሮ፣ አድሏዊ አሰራሮች፣ በአንዳንድ ፖሊሶችና ዳኞች ላይ የሚታየው የሥነ – ምግባር ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በህገ ወጥ የንግድ ወንጀል በህግ ቁጥጥር ስር የሚውሉ ተጠርጣሪዎች አፋጣኝ የህግ ውሳኔ ቅጣት እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ የሚታዩ ውስንነቶችን ጠቁመዋል።
የፀረ ሙስና ተቋማት የሚሰጣቸው የህግ ሽፋን እንዲዳከሙና የተወሳሰበ አሰራር ውስጥ እንዲገቡ መነሻ ሆኗል ብለዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ፋንታዬ በተሳታፊው የተነሱ ሀሳቦች በህግ አተረጓጎም ላይ የታዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ጠቅሰው የህግ አካላት ከምንም በላይ ለህሊናቸው ቢሰሩ ህብረተሰቡም የፍርድ መጓደልና ብልሹ አሰራሮችን ከመታገል አኳያ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።
በማጠቃለያው ወ/ሮ መስከረም የተነሱ ግብዓቶች እጅግ ጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ቀጣይ በጥናት ላይ በተመሠረተ አግባብ ተግባራዊነታቸው ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ወገኔ ብዙነህ በፍርድ ቤቶችና በፍትህ ዘርፍ ተቋማት የሚታዩ ችግሮችንና ውስንነቶችን በዝርዝር በመለየት በድክመቶች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ በዘርፉ ስር-ነቀል ለውጥ በማምጣት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተአማኒነት ያለው ተግባር ይከናወናል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ