በዘንድሮው በልግ ከ10ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝ በጋሞ ዞን የቁጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

በዘንድሮው በልግ ከ10ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝ በጋሞ ዞን የቁጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮው በልግ ከ10ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝ በጋሞ ዞን የቁጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።

የቁጫ ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ም/ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበራ አይካ እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ ከ717ሺህ 590 ኩንታ በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል።

የምርጥ ዘር አቅርቦት ከተመሳሳይ የምርት ዘመን ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አበራ 808 ከንታል ምርጥ ዘር እና 3ሺህ 280 ኩንታል ማዳበሪያ በወቅቱ ቀርቦ ከአፈር ጋር መቀላቀል መቻሉንም በመጠቆም።

የቁጫ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መርዕድ መሰለ በበኩላቸው በወረዳው ባሉት 24 ቀበሌያት በ2016 የበልግ በበቆሎ፣ ለውዝ እና ቦሎቄን ሙሉ ፓኬጅን በመጠቀም አርሶ አደሩ እንዲያለማ መደረጉን ጠቁመዋል።

አክለውም ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በወረዳው በሚገኙ 13 ቀበሌያት በ37 ክላስተር 1ሺህ 800 ሄክታር መሬት በበቆሎ እንደሚለማም ኃላፊው ጠቁመዋል።

እስካሁን በወረዳው 10ሺህ 310 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አቶ መርዕድ ገልፀው  ከዕቅዱ 95 ነጥብ 5 ከመቶ መከናወኑንም ተናግረዋል።

አርሶ አደር ዋለልኝ ገብሩ እና ምስጋናው ዳንኤል በቁጫ ወረዳ የወዘቴ ቀበሌ አርሶ አደሮች ሲሆኑ እያንዳንዳቸው ባላቸው 3 ሄክታር መሬት በቆሎና ለውዝ በመዝራት የአረም ቁጥጥርና ተባይ የመከላከል ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

እንደ አርሶ አደሮቹ ገለፃ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ በመቅረቡ አዝመራው የተሻለ እንዲሆን አድርጓል።

ከተባይ ቁጥጥር እስከ ምርት መሰብሰብ ድረስ አዝመራውን በመንከባከብ የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ እንደሚገኙም በመጠቆም።

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን