ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 6ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉበኤን በዲመካ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የዞኑ ምክር ቤት፣ የአስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ በስፋት ውይይት ተደርጓል።
በትምህርት ጥራትና ውጤት ማሽቆልቆል፣ በየጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት ችግር፣ የፀጥታ ችግር መኖሩ እና በሌሎችም የምክር ቤት አባላት የመከሩ ሲሆን በቀጣይ አስፈፃሚው አካል በልዩ ትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ አካላት ላይም የህግ የበላይነት ተረጋግጦ ተጠያቂነት ሊሰፍን ይገባል ተብሏል።
የመንገድ መሠረተ-ልማት ሥራዎች፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ የመስኖ ተግባራት በዞኑ እንደየአካባቢው ችግሮች መኖራቸው ከቀረበው የአስፈፃሚ መሥሪያ ቤት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ተገንዝቦ መስተካከል እንዳለባቸው ምክር ቤቱ አሳስቧል።
ልማታዊ ሥራዎችን በተሻለ መልኩ ለማከናወን የገቢ አቅም በሚጠበቀው ልክ አለመሆን፣ ሰፋፊ መሬት ለማልማት በኢንቨስትመንት ዘርፍ መሬት ወስደው በአግባቡ የማያለሙ እንዳሉ በኢኮኖሚ ዘርፍ በምክር ቤቱ ተመክሮ በቀጣይ መስተካከል እንዳለበት ውሳኔ ተላልፏል።
የምክር ቤት አባላት በዞኑ በሚተገበሩ ሥራዎች ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንደሚጫወቱም ገልፀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ አጠቃላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ፀጥታን በተመለከተ እየተሠራ እንዳለና ሁሉም ለዚህ ሥራ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ያሳሰቡት አቶ ማዕከል፤ በምክር ቤቱ በድክመት የተገመገሙ ተግባራት በቀሪ ወራት ተሻሽለው ውጤት እንዲመዘገብ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ሎስንዴ ሎኛሱዋ፤ ምክር ቤቶች የሚያነሷቸውና በድክመት እንዲታረሙ ውሳኔ የሚያስተላልፏቸው ወደ ውጤት እንዲቀየሩ አስፈፃሚ አካላት በሙሉ ሀላፊነት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው ጉባኤ የዞኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ካዳመጠ በኋላ በጥልቀት ገምግሟል።
የፍትሕ ሥራዓቱ በህዝቡ ዘንድ አመኔታ እንዲኖረው በግልፀኝነት ሊሠራ ይገባል ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
የደን ውጤቶችን በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባም ለምክር ቤቱ አጀንዳ ቀርቦ ተመክሮበታል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ