የሕብረት ሥራ ማህበራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሪፎርም ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሕብረት ሥራ ማህበራትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሪፎርም ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ ገለጸ።

በአንድ ሺህ መሠረታዊ ማህበራት ላይ ሪፎርም እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 2069 መሠረታዊ ማህበራትና 21 ዩኒየኖች ይገኛሉ።

የሪፎርሙ ዓላማ የሕብረት ስራ ማህበራትን ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፣ የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሳደግ፣ አሰራርን ለማሻሻልና የአባላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሆነ የገለጹት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ ናቸው።

በፌዴራል ሕብረት ስራ ማህበራት አደረጃጀት አዋጅ ቁጥር 788/2009 መሠረት የአንድ ሕብረት ስራ ማህበር የአባላት ቁጥር  50 መሆን ሲገባው  በክልሉ ካፋ ዞን 100፤ ዳውሮ ዞን 267፤ ቤንች ሸኮ ዞን 240፤ ምዕራብ ኦሞ ዞን 33፤ ሸካ ዞን 87፤ እንዲሁም ኮንታ ዞን 61 በድምሩ 788 መሠረታዊ ማህበራት የአባላቶቻቸው ቁጥር ከደረጃ በታች መሆኑ መረጋገጡን ገልጸዋል።

አሁንም ማጣሪያ እየተደረገ ስለሚገኝ ቁጥራቸው ሊጨምር ስለሚችል እንደ ሀገር አምሳ ሺህ መሠረታዊ ማህበራት ላይ ሪፎርም ለማድረግ ከታቀደው ውስጥ እንደ ደቡብ ምዕራብ ክልል አንድ ሺህ መሠረታዊ ማህበራት ላይ ሪፎርም እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

ሪፎርሙ በ2016 በጀት ዓመት ቀሪ ወራት የሚካሄድ ሆኖ በፌዴራል ደረጃ የተሰጠውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ወደ ዞኖች በማውረድ በክልሉ የሚገኙ ስድሰት ዞኖችን በሁለት ጎራ በመመደብ ለግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ መምሪያ ኃላፊዎችና ምክትሎቻቸው ስልጠና መስጠቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ማህበራቱ ካፒታላቸው 800 ሚሊዮን ብር መድረሱን አቶ ቀበሌ ጠቁመው ሪፎርሙ ከተካሄደ በአንዳንድ ዩኒየን አባላት መካከል ከሀብት ክፍፍል ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን አለመግባባት ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን አቶ ቀበሌ አክለው አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን