የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በተገቢው ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ ተጠቆመ

የገጠር መንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ በተገቢው ለመመለስ እየተሠራ እንደሆነ ተጠቆመ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ በክልሉ ጌዴኦ ዞን የመንገድ ልማት ሥራ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በክልሉ ከ1 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገድ፣ የድልድይ ሥራና 6 የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ በያዝነው ዓመት ለማጠናቀቅ እየሠራ እንደሚገኝ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በጌዴኦ ዞን በክልሉ በጀት ከሚሠሩ መንገዶች ውስጥ በገደብ ወረዳ ሐሎ ጨልጨሌ የመንገድ ፕሮጀክት ከ7 ኪሎ ሜትር በላይ መጠናቀቁን የገለጹት የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፤ በክልሉ 1 መቶ 14 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንዳለ ተናግረዋል።

በክልሉ የዚሁ መንገድ አካል የሆኑ ድልድዮችና የመንገድ መሠረተ ልማት ባልወጣበትና ገደላገደሎች ባለበት ተንጠልጣይ ድልድዮችን እየሠሩ እንደሚገኝ ኢንጅነሩ ገልጸዋል።

ማንኛውንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያለመንገድ የማይታሰብ መሆኑን የተረዳው ማህበረሰብ በራሱ አስተዋጽኦ መንገድ በመክፈት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ይደነቃል ያሉት ኢንጅነር ዳግማዊ፤ ተግባሩ በየአካባቢው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በአከባቢያቸው እየተሠሩ ያሉ መንገዶች በራስ አገዝ የሚሠራውን እያሠሩና እየሠሩ እንዳለ የተናገሩት የገደብና የይርጋጨፌ ወረዳ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊዎች አቶ ደሳለኝ ሽፈራውና ኤርሚያስ ሽፈራው ክልሉ የጀመራቸውና መጠናቀቅ ያለባቸው ሥራዎች እንዲጠናቀቁና የማሽን ድጋፍ በሚያስፈልግበት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በመስክ ምልከታው ጥያቄ ያስነሳው በገደብ ወረዳ ከገደብ ጎቲቲ የመንገድ ፕሮጀክት 2015 ዓ.ም ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የቀረው በነዳጅ መናር ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት የደቡብ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አሰኪያጅና የግብአት አቅርቦት ደጋፊ ሥራ ሂደት ወ/ሮ ጌጤነሽ ገብረማሪያም በቅርቡ ከኮንትራክተሩ ጋር በተደረሰ ስምምነት ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

በአከባቢያቸው ከዚህ ቀደም በመንገድ መሰረተልማት ባለመኖር ይቸገሩ እንደነበር የገለጹት ከይርጋጨፌና ገደብ ወረዳዎች ወ/ሮ ካሰች በየነና አቶ ጌቱ ባልቻ አሁን ላይ ከችግሩ ወጥተው ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

በአከባቢያቸው የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲጠናቀቁም ጠይቀዋል።

በመስክ ምልከታው የክልል፣ የዞንና የወረዳ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ካሣሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን