ወጣቶች ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት  ግምባር ቀደም ሚና  እንዲወጡ ተጠየቀ

በቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ የወጣቶች አደረጃጀት ማጠናከርና መልሶ ማደራጀት የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል ።

ሰላምና ደህንነት ላይ ወጣቶችን በማሰማራት ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅድሚያ መሰራት እንዳለበት የገለጹት የቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን አኖ ለዚህም በየመድረኮቹ በማሳተፍ ማወያየት እንደሚገባ አንስተዋል።

በዞኑ ወጣቶች ሰላምን ከማስከበር አኳያ ሰፊ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው በበዓላት ወቅት ያሳዩት ተግባር የሚበረታታ እና የሚደገፍ እንደሆነ በመግለፅ ሁሉም ወጣቶች ለሰላም መቆም  እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የነገ ተተኪ አመራር የዛሬ ወጣቶች ናቸው ያሉት የሶያማ ዙሪያ ወረዳ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሽብሩ ኦቴ ያላቸውን እምቅ ችሎታ እና ክሂሎት በመጠቀም ለነገ ማብቃት ያስፈልጋል ብለው፣ ዛሬ ላይ ያሉ ወጣቶችም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመውሰድ ለሀገር ሰላም እና ልማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የንቅናቄ መድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች እንደተናገሩት፣ ወጣቶች የተሻለ ስራ ሲሰሩ ማበረታታት እና መደገፍ ያስፈልጋል፤  የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ አለባቸው።

የወጣቶች ሊግ፣ ፌደሬሽን እና ማህበር ስም ብቻ ሆነው መቅረት እንደሌለባቸውና  የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላትም ከተሟላ አገልግሎት ጋር ለወጣቶች ክፍት መሆን እንደሚገቡም ወጣቶቹ ተናግረዋል።

 ዘጋቢ : አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን