በኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ ማሽኖችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ በቢሊዮን የሚገመት ኪሳራ ደርሷል

በኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ ማሽኖችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ በቢሊዮን የሚገመት ኪሳራ ደርሷል

ሀዋሳ፡ ሚያዝ 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ያሉ ትላልቅ ማሽኖችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚገመት ሀብት እያጣች መሆኑ ተገለፀ፡፡

ይሄን ችግር ለመቅረፍ ያለመ የአሰልጣኞች ስልጠና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ እየሰጠ ነው።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ተግባር በመካከለኛው ደረጃ የሰለጠኑ ዜጎች በብዛት እና በጥራት ማፍራት ነው። ስራ ጠባቂ ሳይኑ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ቁጥር ከፍ ማድረግም የዚሁ ተቋማ ሀላፊነት ነው።

ተቋሙ ይሄን ሀላፊነት ተሸክሞ እየሰራ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግቡን አሳክቷል ማለት እንደማይቻል የተናገሩት በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪያል ምህንድስና መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር አለማየሁ ተስፋዬ ናቸው ።

ለዚህ ደግሞ ትልቁ ችግር በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች በከፍተኛ ወጪ የተገዙ ማሽኖች ወደ ስራ አለመግባታቸው እና በጥቃቅን ብልሽቶች መቆማቸው የስልጠናው ጥራት ላይ ጥላ እንዳጠላ ተናግረዋል ።

በቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ተቋማት ያሉ ትላልቅ ማሽኖች በቢሊዮን ብር የሚገመት የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ስለመሆኑ ጠቅሰው ይሄንን ሀብት በአግባቡ አለመጠቀም ሀገርን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋት ነው በማለት አስረድተዋል ።

ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የመጡት አሰልጣኝ ሲሳይ ሀይሉ በበኩላቸ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ቴክኒክና ሙና ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተለያዩ ትላልቅ ማሽኖች አሉ ብለው ስራ ያልጀመሩትን ወደ ስራ እንዲገቡ እንዲሁም ብልሽት ያለባቸውን በመጠገን ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በሾኔ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ብቻ ዘጠኝ ማሽኖች ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ያለ ሰራ የቆሙትን ወደ ሰራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሰለሞን ፈርሻ በክልሉ 38 የቴክኒንክና ሙያ እንዲሁም ኢንዱስሪያል ኮሌጆች እንዳሉ ጠቅሰው ተቋማቱ የመለማመጃ ማሽኖችን በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለው እየተሰጠ ያለው የአሰልጣኞች ስልጠናም ይሄን አላማ ከዳር ለመድረስም አውንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ማሽኖቹ ወደ ስራ መግባት ከቻሉ ከፍተኛ ወጪን ለማስቀረት ፣ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን ለመፍጠርና ወደ ኢንዱስትሪው ብቁ ዜጎች ለማስገባት ዕድል ይሰጣል ባይ ናቸው ።

ዘጋቢ : ጀማል የሱፍ