ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሴክተር በ2016 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀምና በቀሪ ወራት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩም በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች የሚገኙ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎችና የዘርፉ አስተባባሪዎች በመድረኩ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አምሪያ ሲራጅ እንዳሉት፥ በዝግጅት ምዕራፍ የክልሉን ቢሮ እና ከክልል በታች በአዲስ የተደራጁ መዋቅሮች የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍን በፍጥነት በማደራጀትና ራሱን በማብቃት “በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ተስፍ ለአዲስ ክልል” በሚል መሪ ቃል በተመሰረተው ክልል በየሴክተሩ የሚሰሩ የሽግግር ተግባራት እንዲተገበሩና በተደረገው ክልል አቀፍ ርብርብ ሴክተሩ ጉልህ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃም የክልሉን ሕዝብ በልማትና መልካም አስተዳደር፣ በሠላምና ፀጥታ ብሎም በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ ሴክተሩ ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የሕዝብ ለሕዝብ አንድነትንና አብሮነትን ለማጎልበት፣ የብሔራዊ አንድነትና የገዥ ትርክት የበላይነት ለማስጠበቅ፣ ሕዝቡ የመንግስት አቅጣጫዎች ላይ በቂ መረጃ እንዲያገኝ እንዲሁም መንግስትም የክልሉን ሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ለመለየት የሚያስችል የተደራጀ መረጃ እንዲያገኝ በበጀት ዓመቱ በትኩረት እንደተሰራ ተናግረዋል።
በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የክልሉን ሕዝብና መንግስት የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው፥ የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ክልሉ አሁን ላለበት ተግባር ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
ሚዲያው ከፍተኛ አቅም እንዳለው የተናገሩት ዋና አማካሪው በተለይ አሁን ባለንበት ወቅት የኮሚዩኒኬሽን አስፈላጊነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ብለዋል።
አሁን ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና እውቀት ከዘርፉ ይጠበቅበታል ያሉት አቶ ንጉሴ፥ በቀጣይም ቀሪ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ቃልአብ ፀጋዬ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ