በማህበር ተደራጅተው መስራት በመቻላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ወጣቶች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ።

ወጣቶቹ በቀጣይ ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ እና ማሽኖችን ለማምጣት መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

“ጉዞ ለለውጥ የአንድ ቀን ጫጩት ማህበር” ሰብሳቢ ወጣት በቃኸኝ ለማ የመጀመሪያ ድግሪ ተመራቂ ቢሆንም፥ ተቀጥሮ ከመስራት ይልቅ በማህበር በመደራጀት በግል ስራ ውጤታማ መሆኑን በመገንዘብ የአንድ ቀን ጫጩት በማምጣት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግሯል።

ወጣት በቃኸኝ ጠንክሮ በመስራት ያገኘውን ገቢ በመቆጠብ ሶስት የከተማ ቦታ ላይ ቤት በመስራት፣ ሁለት ባለ ሶስት እግር ሞተር፣ ሁለት ባለሁለት እግር ሞተር በመግዛት እንዲሁም በባንክ ከ600 ሺህ ብር በላይ በመቆጠብ አጠቃላይ ካፒታል ሁለት ሚሊየን ብር ማድረሱን ገልጿል።

በማህበሩ አምስት አባላት መኖራቸውን ገልጾ ሶስቱ በሀብት ደረጃ ከእሱ ጋር የሚፎካከሩ መሆናቸውን ጠቅሷል።

ማህበሩ በቀጣይ መፈልፈያ ማሽን ለማምጣት ከልማት ባንክ ጋር በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።

ወጣት ዮሴፍ ዱልጌ በቡልቂ ከተማ ወተት አምራችና አከፋፋይ ሲሆን ከአንድ ጥጃ ወደ አራት ላምና አራት ጥጃ ማደጉን ተናግሯል። አሁን ወተት በአማካይ በቀን 30 ሊትር በማምረትና 120 ሊትር ከተለያዩ አከባቢዎች በመሰብሰብ ወደ ሌሎች አከባቢ እንደሚያከፋፍል ገልጿል።

ጉያ ምንጭ ወተትና ጁስ ስራ ማህበር ሰብሳቢ ፍቃዱ በየነ ለአምስት ሆነው በ130 ሺህ ብር ካፒታል ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግሮ የወሰዱትን ብድር በአግባቡ መልሰው፥ በ300 ሺህ ብር የማስፋፊያ ስራ መስራታቸውን ተናግሯል።

ወጣቱ በቀጣይ በአከባቢው በቂ ምርት በመኖሩ የዘይት መጭመቂያ እና ከአቦካዶ ምርት የተለያዩ ቅባቶችን ለመስራት ማቀዳቸውን ገልጾ የወረዳው መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን  እንዲያመቻችላቸው ጠይቋል።

በጎፋ ዞን የቡልቂ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይሁን ደምሴ በ2016 ዓ.ም 1ሺህ 128 ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 726 ስራ ፈላጊዎች ከስራ ጋር መገናኘታቸውን አብራርተዋል።

በከተማው ከ20 በላይ ማህበራት ተጨማሪ የማስፋፊያ እና የገንዘብ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸው የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ከማዘጋጃ ቤት፣ ከኦሞ ባንክ፣ ከልማት ባንክ እና ደቡብ ግሎባል ባንክ ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን