ዛሬ ምሽት በሩብ ፍፃሜው አርሰናል ከ ባየርን ሙኒክ እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ከ ሪያል ማድሪድ የሚያከናውኑት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል

ዛሬ ምሽት በሩብ ፍፃሜው አርሰናል ከ ባየርን ሙኒክ እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ከ ሪያል ማድሪድ የሚያከናውኑት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል

ሀዋሳ፡ ሚያዚያ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ የሩብ ፍፃሜ መርሐግብር አርሰናል በኤምሬትስ ባየርን ሙኒክ እንዲሁም ሪያል ማድሪድ በኤልሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ማንቸስተር ሲቲን ዛሬ ምሽት ያስተናግዳሉ፡፡

በጥሎ ማለፉ ፖርቶን በመለያ ምት አሸንፎ ከ14 ዓመታት በኋላ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለው አርሰናል በጠንካራ ወቅታዊ አቋም ላይ ሆኖ ባየርን ሙኒክን ይገጥማል።

አርሰናል በተለይም የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት (2024) ከገባ ወዲህ አስደናቂ የሆነ ስኬታማ ጉዞን በማድረግ ላይ ይገኛል። ክለቡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል 10 በማሸነፍ ማግኘት ከሚገባው 33 ነጥብ 31 ማሳካት ችሏል። በነዚህ ጨዋታዎች 38 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ ሲያሳርፍ 5 ጎሎችን ብቻ ነው ያስተናገደው።

በአንፃሩ 6 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ ዋንጫን ያነሳው ባየርንሙኒክ በቡንደስሊጋው ለ11 ተከታታይ ዓመታት ተቆናጦ የቆየውን ክብሩን በባየር ሊቨርኩሰን ሊነጠቅ የአንድ ጨዋታ ዕድሜ ብቻ ቀርቶት በሻምፒንስሊጉ ሩብ ፍፃሜ ዛሬ ምሽት ከአርሰናል ጋር ይጫወታል።

የባቫሪያኑ ክለብ በቡንደስሊጋው ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶችን ካስተናገደ በኋላ ነው የሰሜን ለንደኑን ክለብ ከሜዳው ውጪ የሚገጥመው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በቦሩሲያ ዶርትሙንድ 2ለ0 እንዲሁም በሄይደንሄይም 3 ለ 2 በሆነ ውጤት መረታቱ ይታወሳል።

በጀርመን ሱፐር ካፕ በፍፃሜው በአርቢ ሌይፕዚች እና በጀርመን ዲኤፍቢ ፖካል ዋንጫ በ2ኛው ዙር በሳርብሩኸን ተረቶ ከውድድሩ ውጪ የሆነው ባየርን ሙኒክ ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የውድድር ዓመቱን ያለ ዋንጫ ላለማጠናቀቅ ብቸኛ የዋንጫ ተስፋ በሆነው ሻምፒዮንስሊግ ላይ ሙሉ ትኩረቱን በማድረግ እንደሚጫወት ተገምቷል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ 12 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባየርን ሙኒክ 7 ጊዜ ሲረታ አርሰናል ደግሞ 2 ጊዜ አሸንፏል። ቀሪ 2 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።

የመጨረሻ 3 የእርስ በእርስ ግንኙነቶችን ባየርን ሙኒክ በተመሳሳይ 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ አይዘነጋም።

በአጠቃላይ የሁለቱ እርስ በእርስ ግንኙነቶች ባየርን ሙኒክ 27 ጎሎችን በአርሰናል መረብ ላይ ሲያሳርፍ አርሰናል 13 ጎሎችን ነው ባየርን ሙኒክ ላይ ማስቆጠር የቻለው።

እኤአ በ1998 ከፈረንሳዩ እግርኳስ ክለብ ሌንስ ጋር የመጀመሪያውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ ጨዋታውን ያከናወነው አርሰናል በውድድር መድረኩ 200ኛ ጨዋታውን ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜዳው ከጀርመኑ ክለብ ጋር ያከናውናል።

ያለ ደጋፊ ከሜዳው ውጪ በሚጫወተው ባየርን ሙኒክ በኩል ባለፈው ክረምት ከቶትንሃም የተዛወረው ሃሪ ኬን እንግሊዝን ለቆ ወደ ጀርመን ከተጓዘ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኤምሬትስ አቅንቷል።

የቶቴንሃም ሆትስፐርስ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አስቀጣሪው ሃሪ ኬን በሰሜን ለንደን ሳለ ከአርሰናል ጋር በሁሉም ውድድሮች 19 ጊዜ ተገናኝቶ 14 ኳሶችን ከመረባቸው ጋር አዋህዷል።

በአርሰናል በኩል ጉዳት ላይ የሚገኘው ዩሪያን ቲምበር ከምሽቱ ጨዋታ ውጪ የሆነ ብቸኛው ተጫዋች ነው።

በባየርን ሙኒክ በኩል ግብ ጠባቂው ማኑኤል ኑየርን ጨምሮ ጉዳት ላይ የነበሩት ሌሮይ ሳኔ፥ኪንግስሊ ኮማን፥ናስር ማዝራዊ እና አሌክሳንደር ፓቭሎቪች ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ተነግሯል።

በሌላ በኩል ሪያል ማድሪድ በሜዳው ማንቸስተር ሲቲን በሜዳው የሚያስተናግደው ጨዋታ ሌላኛው የምሽቱ ተጠባቂ መርሐግብር ነው።

ለሦስተኛ ተከታታይ ውድድር ዓመት በሻምፒዮንስሊጉ የሚገናኙት ሁለቱም ክለቦች በሊጎቻቸው ጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ሆነው ይገናኛሉ።

ባለፈው ዓመት በታሪኩ የመጀመሪያውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ ዋንጫን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ ክብሩን ለማስጠበቅ የ14 ጊዜ የሻምፒዮንስሊግ ዋንጫ ባለክብሩን ምሽት ላይ በስፔን ርዕሰ መዲና ይገጥማል።

ከክለቦቹ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች በተጨማሪ በሻምፒዮንስሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን በመምራት አንጋፋ በሆኑት ካርሎ አንቾሎቲና ፔፕ ጋርዲዮላ መካከል የሚደረገው የታክቲክ ጦርነትም በእጅጉ ይጠበቃል።

በሪያል ማድሪድ በኩል ለረጅም ወራት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የቆየው ኤደር ሚሊታኦ ለጨዋታው መድረሱ ሲገለፅ ግብ ጠባቂው ቲባውት ኮርቶዋ እና ዳቪድ አላባ ግን በምሽቱ ጨዋታ አይሳተፉም።

በማንቸስተር ሲቲ በኩል ካይል ዎከር እና ናታን አኬ በጉዳት ምክንያት፤ ወደ ስፔን ባቀናው ስብስብ አለመካተታቸውን ክለቡ አሳውቋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ