የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው 1ሺ 445ኛውን የዒድ አል-ፈጥር በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በዓሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት የዘንድሮዉን የ1ሺ 445ኛዉን የዒድ አል_ፈጥር በዓል ስናከብር በአዲስ ክስተትነት ከምናነሳቸዉ ጉዳዮች አንዱ አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መንግታዊ ተልዕኮዉን በይፋ በጀመረ በወራት ዕድሜ ዉስጥ ሆነን የምናከብረዉ በዓል በመሆኑ በዓሉን ከወትሮዉ የተለየ ገፅታ ያላብሰዋል ብለዋል።
የዘንድሮዉን የረመዷን ወር ፆም በየአካባቢያችን በጋራ የኢፍጣር ስነ ስርዓቶች አጅበን የተጓዝንበት ድባብ ደማቅና ትዉስታዉም አብሮን የሚቆይ እንደሆነ ይሰማኛል ሲሉ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የገለጹት።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ‘ብዝሃነታችን ዉበታችንና በረከታችን ነዉ’ የሚለዉን መንፈስ መሠረት አድርገን የኢፍጣር ማዕዶችን በህብረት ተቋድሰናል፤ የአብሮነትን መንፈስ አድሰናል፤ የመተባበርን፣ የመከባበርን፣ የመተሳሰብን እሴት ለማጎልበት ጥረት አድርገናል ሲሉም ጠቁመዋል።
ይህ ድንቅ ማህበራዊ መስተጋብር ብዝሃነታችንን የማክበርና የማስተናገድ የአብሮነት መንገድ ከመሆኑ ባሻገር፣ የወንድም/እህትማማችነትን እሴትን ለማጠናከር አጋዥ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በረመዷኑ የታየዉ የመተሳሰብ፣ ተካፍሎ የመብላትና የመረዳዳት ተግባርም ቀጣይነት ሊኖረዉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያዊነት በፈሪሀ ፈጣሪ በረከት የተሞላ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴት የገነባው በወንድም/ እህትማማችነት እሴት ላይ የተመሠረተ ነዉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ድንቅ ትዉፊትና እሴት ማክበርና ማስተናገድ ይጠበቅብናል ሲሉም አስረድተዋል።
ብዝሃነታችንን ዕድልና ምንዳ አድርገን ለሕብረተሰባዊ ለዉጥ ማሳለጫነት ማዋል አለብን።
ብዝሃነትን የመረዳት፣ የማክበርና የማስተናገድ ባህልን ማጎልበት ለዘላቂ ሠላም፣ ለጋራ ልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ለዚህ እሳቤ መዳበር መላዉ የክልላችን ሕዝቦች የየበኩላችሁን እንድታበረክቱ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
ከልዩነቶቻችን ይልቅ አብሮነታችንን የሚያፀኑ ዘርፈ ብዙና ዘመን ተሻጋሪ መስተጋብሮች ያስተሳሰሩን ሕዝቦች ነንና በጋራ እዉነቶች፣ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ የተመሠረት የብሔራዊነት ሥነ ልቦናንና ትርክትን ለማስረፅና ለማፅናት ኃላፊነታችንን እንወጣ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለዘላቂ ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ግንባታ በጋራ እንሥራ ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም የዒድ አል_ፈጥር በዓል እንዲሆንላችሁ በድጋሚ እመኛለሁ ብለዋል።
ዒድ አል_ፈጥር ሙባረክ!
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ