የደቡብ ኢትዮጲያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለ1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ1445ኛው የዒድ አል ፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ!
ዒድ አል ፈጥር በእስልምና እምነት ተከታዮች ልዩ ትርጉም ያለው የቅዱሱ የረመዳን የፆም ወር ማሳረጊያ ታላቅ በዓል ነው፡፡
ዕለቱ ሕዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱና በታላቁ የረመዷን ወር ለሀገራችን ሰላምና ፀጋ፤ ለመላው ህዝባችን ፍቅርና አንድነት ወሩን ሙሉ በፆምና በዱአ አሳልፎ ከፈጣሪ እዝነትና በረከት የሚቀበልበት ልዩ ቀን ነው፡፡
የዒድ አል ፈጥር በዓል የመተሳሰብና የመጠያየቅ፤ የመረዳዳትና የአብሮነት በዓል ነው፡፡ በዓሉ ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያደርገው እንደነበረው በአንድነት ተሰባስቦ ያለው ለለሌው በማካፈል ማህበራዊ ትስስሩን ይበልጥ አጠንክሮ በአብሮነት የሚያከብረው በዓል ነው።
አንድነትና ኅብረት፤ መደጋገፍና መረዳዳት በእስልምና ልዩ ስፍራ እንደሚሰጠው የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን የበርካታ ዕሴቶች ባለቤት የሆንን ህዝቦች ብቻ ሳንሆን ልዩነቶቻችን የኅብር ማንነትን ውበት ያጎናፀፉን ድንቅ ህዝቦች ነን፡፡
በአሁኑ ወቅት በኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት አንድነታችንን አጽንተን የዘመናት ጠላታችን የሆነው ድህነትና ኋላ ቀርነት ታርክ የማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
ይህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረታችንን እና መደጋገፋችንን የሚፈልግ በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙም የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሰረት በመተጋገዝና አብሮ በመስራት ለጋራ ቤታችን ዘላቂ ሰላም፤ ዕድገት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ይበልጥ መትጋት ይገባዋል።
በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር ለዘመናት የገነባነውን የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመደጋገፍ እሴት በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ጉዟችንን ከዳር ለማድረስ በየተሰማራንበት ዘርፍ ሀገራችንን በሐቀኝነት በማገልገል የድርሻችንን እየተወጣን እንዲሆን ስል አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።
ዒድ ሙባረክ!
ፈጣሪ ሀገራችንን እና ሕዝቦቿን ይባርክ!

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ