እንኳን ለ1445ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ፡፡
የረመዳን ወር መላው ሙስሊም ማኅበረሰብ በናፍቆትና በጉጉት የሚጠብቀው ወር ነው። ወሩ የአሕዛብ በሮች የሚዘጉበት፣ የጄነት በሮች ወለል ብለው የሚከፈቱበት ነው። ሙስሊሙ በጾምና በኢባዳ ከፈጣሪው ጋር የሚቀራረብበት፣ ዚክር የሚበዛበት፣ በጎነት የሚጎላበት፣ የምሕረትና የመባረክ ወር ነው ረመዳን።
የጨረቃን ዑደት መሠረት አድርጎ በተዘረጋው ባለ ዐሥራ ሁለት ወር የሂጀሪያ የዘመን አቆጣጠር፣ ቅዱሱ የረመዳን ወር ከሻባን ወር ቀጥሎ ይመጣል። የጽድቅ ወሩ ረመዳን እስኪመጣ ሙእሚኑ ዐሥራ አንድ የመፈተኛ ወራትን ያሳልፋል። ረመዳን እስኪመጣ ብዙ መታገሥ፣ ለመልካም ሥራ አብዝቶ መታገል ይጠበቃል።
መጋቢት እንደ ረመዳን ነው፡፡ የመጋቢት ለውጥ የወለደው አዲሱ የተስፋ ብርሃን እስኪመጣ ብዙ ፈተና፣ ብዙ ውጣ ውረድ፣ ብዙ ትዕግሥት ጠይቆ ነበር። ከዐሥራ አንድ ወራት በኋላ የረመዳን መምጣት አይቀሬ እንደሆነው ሁሉ፣ ለውጡም አይቀሬ ነበር። ጊዜው የደረሰን ሐሳብ ሊያስቆመው የሚችል ምድራዊ ኃይል የለምና። ጨለማ ምን ቢረዝም የቀኑን ብርሃን ማስቀረት አይችልም፡፡ ተሸንፎ ለብርሃን ይለቃል፡፡ ስድስት ወር ሙሉ ጨለማ የሚገጥማቸው የሰሜንና የደቡብ ዋልታ አካባቢዎች እንኳን ይሄንን እውነት ይመሰክራሉ።
የረመዳን ወር ሁለት ዓይነት ተግዳሮት አለበት፡፡ ከመምጣቱ በፊት ረጅም የ11 ወራት ተግዳሮት አለበት፡፡ ከመጣ በኋላ ደግሞ የበረከትና የዕዝነት ጾም እንዳይሆን ሸይጣን ሌላ ፈተና ያመጣበታል፡፡ እውነተኛ አማኝ ሁለቱንም ተቋቁሞ በጽናት ያልፋል፡፡ የመጋቢት ለውጥም እንደዚሁ ነው፡፡ ከመምጣቱ በፊት አያሌ ዘመናትን ሲጠበቅ፣ ሲናፈቅ ኖሯል፡፡ የብዙ ትውልድን መሥዋዕትነት ጠይቋል፡፡ ከመጣ በኋላ ደግሞ ሀገር እንዳትለወጥና እንዳትበለጽግ በሚፈልጉ ኃይሎች አያሌ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ አስገራሚ የማይሆነው ነገር፣ ሁለቱም ተግዳሮቶች የሚፈትኑ፤ ግን የሚሸነፉ ተግዳሮቶች መሆናቸው ነው፡፡
በዚህ ዓመት ያሳለፍነው የረመዳን ወር ሰላማዊ፣ አያሌ ድኾችንና ችግረኞችን ያገዝንበት፤ እርስ በርስ የተደጋገፍንበት፣ የተለያዩ እምነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በጽናት ያሳዩበት ወር ነበር፡፡ እነዚህ ለመንገዳችን የመብራት ምልክቶች ናቸው፡፡ የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በአንድነት ሆነን ልናልፋቸው እንደምንችል ያስገነዝቡናል፡፡ ‹ብልህ ሰው ረመዳንን እስከ ረመዳን ያቆየዋል› የሚል አባባል አለ፡፡ በረመዳን ጾም ጊዜ ያገኘውን በረከት፣ መንፈሳዊ ኃይልና ጠላትን ድል የማድረግ ዐቅም እስከሚቀጥለው ረመዳን ድረስ ይጠቀምበታል፡፡ ወደኋላ አይመለስም እንደማለት ነው፡፡
እኛም በመጋቢት ለውጥ ያገኘናቸውን ዕሴቶች ብልጽግናችንን እስከምናረጋግጥበት ቀጣይ ምእራፍ ድረስ ይዘናቸው ልንዘልቅ ይገባል፡፡ ሰላም፣ ይቅርታ እና ፍቅር ዕሴቶቻችን ናቸው፡፡ በፍቅር መደመርና በይቅርታ መሻገር ዋናው መርሐችን ነው፡፡ ታሪካዊ ስብራቶችን መጠገንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጽናት ራእያችን ነው፡፡ መደመር መንገዳችን፣ ብልጽግና መዳረሻችን ነው፡፡ እነዚህ ዕሴቶች በለውጥ ዘመን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች የምንወጣባቸውና እስከቀጣዩ መዳረሻ የምንዳረስባቸው ናቸው፡፡ ያም መዳረሻ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው፡፡
በድጋሚ መልካም የኢድ አልፈጥር በዓል ይሁን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ