በፍትህ ተቋማት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የአሰራር ስልቶችን ከመቀየስ ባሻገር ሪፎርሙን መተግበር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በፍትህ ተቋማት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የአሰራር ስልቶችን ከመቀየስ ባሻገር ሪፎርሙን መተግበር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ተቋማት ሪፎርም የስትሪንግ ኮሚቴ የውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ እንደገለጹት፤ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ አካላት ሪፎርም ከዚህ ቀደም በፍትህ ስርዓቱ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረምና የፍትህ ተደራሽነትን ለማሳደግ ይረዳል።

አፈ ጉባኤዋ አክለውም በዘርፉ የሚስተዋለውን የአገልግሎት ጥራት ከማሳደግ ባሻገር ቅሬታዎችን በሂደት ለመፍታት ሪፎርሙን በበላይነት የሚመራው የስትሪን ኮሚቴ ከፍተኛ ሀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ወደራስ በመሳብና የአሰራር ስልት በመቀየስ በፍትህ ተቋማት ላይ የሚነሱ ችግሮችን ፈጥኖ ማረም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በታማኝነት፣ ህግና ስርዓትን በመከተል በዕውቀት ሪፎርሙን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረው የህዝብን አመኔታ ከፍ ማድረግ ያሻልም ብለዋል አፈ ጉባኤዋ።

በተባበረ ክንድ ፍትህ ላይ ያለውን ጥማት ለማርካት ያለንን ዕውቀት ተጠቅመን በሀላፊነት ልንሰራ ይገባልም ሲሉ ገልፀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ በበኩላቸው አሰራርን ከማዘመን ባሻገር ችግሮቻችንን በመለየት ቀልጣፋ አሰራርን በፍርድ ቤቶች ማስፈን ያሻል ነው ያሉት።

እንደ አገር የፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው እንደ ክልልም እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ተቋማት የራሳቸውን ባህሪ ይዘው ችግሮችን እንዲፈቱና ቀጣይነት ያለው ለውጥ እንዲያስመዘግቡ ማገዝ ያስፈልጋል ተብሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን  ክልል አቀፍ ስትሪንግና ንዑሳን ኮሚቴ ቅንጅታዊ አሰራር ማስፈፀሚያ ሰነድ ቀርቦ አስተያየትና ሀሳብ ተሰንዝሯል።

በፍትህ ዘርፍ ያሉ ጠንካራ ጎኖችን በማሳደግና ደካማ ጎኖችን በማረም የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

በውይይት መድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳን ጨምሮ የፍትህ ዘርፍ ተቋማት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን