በአዋጆች ላይ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ከኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በፀደቁ ሁለት አዋጆች ላይ ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት የአየር ብክለትን ለመቋቋም የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ህዝብን በማንቃትና በማሳተፍ መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሆን እንደሚገባ ተመልክቷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ እንደገለፁት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ከሀገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ጋር በማጣጣም ዜጎች በንፁህ ጤናማ አካባቢ የመኖር መብታቸውን ማረጋገጥ ይገባል።
በተለይም ደግሞ በአየር፣ በውሃ፣ በኘላስቲክና በአፈር ብክለት እንዲሁም በአደገኛ ቆሻሻ የሚወጣውን አለማቀፋዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት መቋቋም ይቸገራሉ ያሉት የቢሮ ኃላፊው የህግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ህዝብን በማንቃትና በማሳተፍ መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአዋጆች ላይ በቂ ግንዛቤ በመውሰድ ንጹሕና ጤናማ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የአካባቢ ብክለትን የምንቆጣጠር አምባሳደሮች መሆን ይጠበቅብናልም ሲሉ አሳስበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እንደ ሀገር ”ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ቃል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ ብክለትን እንከላከል ንቅናቄ መጀመሩ የሚታወስ ነው ብለዋል።
በክልላችን ይህን መነሻ በማድረግ ተመሳሳይ ንቅናቄ የሚጀመር በመሆኑ ሁላችንም ለንቅናቄው ስኬት ንቁ ተሳታፊ መሆን አለብን ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የብክለት ቁጥጥር ሥራ በምን አግባብ መከናወን አለበት? ማንስ ሊቆጣጠረው ይገባል? የሚሉትና ሌሎችም ብክለትን አስመልክተው የተዘጋጁ ርዕሰ ጉዳዮች በመድረኩ በገለፃ ቀርበዋል።
በመድረኩ በክልሉ የሚመለከታቸው አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ