የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ባለፉት ስምንት ወራት በተከናወኑ የHIV/AIDS መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት የአፈፃፀም ግምገማ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በዞኑ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ቢሆንም ቫይረሱ ዛሬም በርካታ ተፅዕኖዎችን እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ የተገኙ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መላኩ ተረፈ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከመንግስት ሰራተኞች የሚቆረጠው የ0.5 በመቶ መዋጮ ለታለመለት አላማ እንዲውል በየደረጃው የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ሀላፊዎች በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዞኑ የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጤና መምሪያው ከሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፁት የዞኑ ጤና መምሪያ ተወካይ አቶ ማርቆስ ፎላ በበኩላቸው፤ በዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በተለየ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ የዘርፈ ብዙ ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስዩም ከበደ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ጉዳት የመቀነስ ሀላፊነት የሁሉም አካል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመግታት በተለይ የሀይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መዝናኛ ማዕከላት፣ ሆቴሎችና የማረሚያ ተቋማት ያላቸውን ከፍተኛ ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በህብረተሰቡ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው መዘናጋት ለቫይረሱ ስርጭት ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ ስለሆነ ይህንን ለመግታት የግንዛቤና የመከላከያ ስራ በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባልም ተብሏል።

በመድረኩ የተገኙ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት በዞኑ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ሚና በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ዶላንጎ – ከዋካ ጣቢያችን