በዘንድሮው የበልግ እርሻ ወቅት 5 ሺህ 300 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ምርት መሸፈኑን የባስኬቶ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ

በምርቱ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በበኩላቸው የገበያ ትስስር፣ የመንገድና ባካባቢው አልፎ አልፎ የሚከሰተው የጸጥታ ችግር ከወዲሁ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

የባስኬቶ ዞን ከቅመማ ቅመም እና ከስራስር ምርቶች በተጨማሪ የቅባት እህሎችን በስፋት ለማምረት የሚያመች የአየር ጸባይና ምቹ ስነ ምህዳር ያለው አካባቢ ነው።

በዞኑ አንግላ ተብሎ በሚጠራው የሰሊጥ ክላስተር አካባቢ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው የበልግ እርሻ የተዘራው ሰሊጥ የቡቃያው አያያዝ እጅግ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚከሰተው የጸጥታ፣ የመንገድ እና የገበያ ትስስር ችግር ከወዲሁ ስጋት የፈጠረባቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት እዲሰጠው ጠይቀዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰሊጥን በልዩነት የሚያጠቃ ተባይ አልፎ አልፎ እየተከሰተ እንደሆነ የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ ግብርና መምሪያው አፋጣኝ እልባት እንዲያበጅ አሳስበዋል።

የግብርና መምሪያው የሰብል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘላለም ኪዳኔ በበልግ እርሻ ወቅት 5 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥን ለማምረት ዕቅድ መያዙን ገልጸው 90 በመቶ መሳካቱንም አብራርተዋል።

የባስኬቶ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንዳፍራሽ ንጉሴ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ከዋጋ እና ከተባይ አኳያ ላነሳቸው ችግሮች ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ፍሬው ፍሻለው የመንገድና የጸጥታ ችግሮችን ከክልሉ መንግስትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን