ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ-ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!! – ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
ሀዋሳ፡ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢፌዲሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ-ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
ሙሉ መልዕክቱም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
አይዴ ጫምባላላ /Ayidde Chamabalalla!!
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ-ጨምበላላ ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ ትልቅ ባህላዊ እሴቶች ያሉት በዓል ነው፡፡
እነዚህም እሴቶች የብሔሩን ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነት እንዲሁም ቀደምት ስልጣኔን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡
የፊቼ-ጫምባላላ በዓል በውስጡ ከያዛቸው እሴቶች የተነሳ በዓለም የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ ሊመዘገብ ችሏል፡፡
ፊቼ-ጫምባላላ የሲዳማ ብሔር አዲስ ዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥምና ክዋኔዎች አሉት።
የፊቼ-ጫምባላላ በዓል አባቶች ደቂቃን፣ ሰዓታትን፣ ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን ቆጥረው ምንም ሳይዛነፍ በየዓመቱ እያከበሩ ያመጡት የሲዳማ ብሔር ሀገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡
ፊቼ-ጫምባላላ በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ሳይንሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው የአለም ቅርስ ነው።
በዚህ በዓል ላይ በክብር እንግድነት ጥሪ የተደረገላቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና የባህልና ቋንቋ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ሀዋሳ ገብተዋል።
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዓሉን በጋራ ከማክበር ያለፈ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባርና ሀላፊነት ውስጥ ፊቼ-ጨምባላላን እና መሰል ባህላዊ እሴቶችና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸውን የህዝብ በዓላትን መጠበቅና ማልማት እንደመሆኑ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው።
ከዚህ አንጻር ተቋሙ እነዚህ በዓላት እንዲጠኑ፣ እንዲለሙ፣ እንዲጠበቁ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማስቻል እንዲሁም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።
ዛሬ በባህል አዳራሽ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ሲሆን ፊቼ-ጨምባላላ ዙሪያ የተጠኑ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እንዲሆን ይመኛል።
መጋቢት 27/2016 ዓ.ም /ሀዋሳ/
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ