ሀዋሳ፡ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ በመንከባከብ የከባቢ አየር መዛባት ችግሮችን መከላከል እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት “የደን ጥበቃ፣ አጠቃቀምና አገርበቀል ዛፎች ምዝገባ” በሚል መሪ ቃል በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ በጨልባ ቀበሌ ተካሂዷል።
የይርጋጨፌ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ሎሌ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ደን በጌዴኦ ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ትርጉምና እንክብካቤ የሚሰጠው ከመሆኑም በላይ ከሰው ልጅ ሕልውና ጋር የሚያያዝ ታሪክ እንዳለውም አውስተዋል።
በዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ለዘመናት ሳይታረሱ የቆዩ ተራራማ ቦታዎችን በደን ለመሸፈን ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው፥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በፍራፍሬ ዛፎች ልማት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በወረዳው ብሎም በዞኑ ሊጠፉ የተቃረቡ ነባር ዛፎችን በአዲስ መልክ ለመተካት እየተተገበረ ላለው ሥራ የሚረዳ የጉድጓድ ዝግጅትና ችግኝ የማፍላት ሥራ በየቀበሌው በተመረጡ ቦታዎች እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ክፍሌ ጅግሶ የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ በተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ችግርና በደን ጭፍጨፋ ሳቢያ የዓለምአቀፍ የአየር መዛባት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውሰው ለዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም አስረድተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ለአግሮ-ፎረስትሪ ልማትና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉና ለመሬት ለምነት ወሳኝነት ያላቸው የዛፍ ዝርያዎችን ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በመናበብ እያቀረቡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፥ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ሀገር በቀል የዛፍ ዝሪያዎችን በመትከል የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ በመንከባከብ የከባቢ አየር መዛባት ችግሮችን መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ብክለት ተጋላጭነት መከላከያ ፍቱን መድኃኒት አግባብነት ያለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የወረዳው አርሶአደሮችም በአየር ንብረት ተጋላጭነት መንስኤዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የወረዳ አስተዳደሩና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ሁሉ ተቀናጅተው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሠሩበት እንደሚገባም አብራርተዋል።
በወረዳው በጨልባ ቀበሌ የተጀመረው የደን ችግኝ ተከላ መርሐግብር ቀጣይነት ባለው መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተዳደሩ በአስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው አቶ ተስፋዬ የተናገሩት።
የጌዴኦ ዞን እርሻና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ በበኩላቸው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር በሕብረተሰቡ ዘንድ ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አኩሪ ትውፊት መሆኑን በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው የደን መጨፍጨፍ በሁሉም ዘንድ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የተፈጥሮ ሃብት መመናመን በዞናችን የብዝሃ-ሕይወት ሕልውናን አደጋ ላይ እየጣለ የሚገኝ ጉዳይ በመሆኑ የፖለቲካ የትኩረት አቅጣጫ አድርገን እየሠራንበት እንገኛለን ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከውይይቱ በቂ ግንዛቤና ልምድ ማግኘታቸውን ገልፀው ለአካባቢውና ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ