የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሄደ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል፡፡

የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወይንሸት ሞላ በንግግራቸው ምክር ቤቱ የህዝቡን መልካም አስተዳደርና  የልማት ጥያቄዎች በተገቢው ምላሽ እንዲያገኙ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በየሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን በመለየት በየደረጃው ምላሽ እንዲያገኙ ከማድረግ አኳያ ቋም ኮሚቴው የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን ማህበራዊ ህይወትና ጤና ላይ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙ  ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ተግባር ውስንነት ችግር ለመቅረፍ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አንስተዋል።

ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተግተው እንደሚሰሩም ወይዘሮ ወይንሸት አረጋግጠዋል።

በጉባኤው የዞኑ አፈጉባኤ ጽህፈት ቤት፣ የዞኑ አስተዳደር ምክርቤት እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ6 ወር  አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ወይይት ተደርጎበታል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ባለፉት  ግዜያት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በጤና ዘርፍ ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የተሰጠው ትኩረት ለውጥ የታየበት ነው በማለት የንጹህ መጠጥ ውሃ  ተደራሽነት አንፃርም ሰፊ ስራዎች መሰራቱን አክለዋል።

በግብርናውም ዘርፍም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ናቸዉ ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የበልግ እርሻ ልማት ከ12.7 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርታ ለማግኘት ከታቀደው ከ11.8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

የዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ባለፉት በስድስት ወራት ውስጥ ከ55ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አብራርተዋል።

ከገቢ  አሰባሰብ ሥራ በተመለከተ ባለፉት 8 ወራት ውስጥ  ከ1.97 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን እንደጠናካራ ጉን አንስተዋል።

በቀጣይም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው  በአጽንኦት ተናግረዋል።

ጉባኤው የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ፣የሥራ አጥነት ችግሮች ለመፍታትና በኦዲት የተገኙ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ አመላለስ ላይ ከፍተኛ ውስንነቶች መኖሩን አንስተው በመምከር በቀጣይ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ትግል ማድረግ እንዳለባቸው  አቅጣጫ በማስቀመጥ   እና  የተለያዩ  ሹመቶችን  በመስጠት  ተጠናቅቋል ።

   ዘጋቢ፡ በቀለች  ጌቾ – ከዋካ ጣቢያችን