በምክር ቤቱ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መላሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

በምክር ቤቱ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መላሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዞኑ ምክር ቤት አባላት ለሚያነሱት የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሀዲያ ዞን ምክር ቤት አባለት ጠየቁ።

የዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት 22ኛ መደበኛ ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።

የሀዲያ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉበኤ ወ/ሮ እቴነሽ ሙሉጌታ ጉባኤውን በንግግር ሲከፍቱ ምክር ቤቱ ከመደበኛ ስራ ጎን ለጎን በቋሚ ኮሚቴ አማካይነት የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችንና የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን በአካል ወርዶ በመከታተል ጉድለቶችን በመሙላት ለህብረተሰቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ አቅጣጫ ማስቀመጡን አንስተዋል።

ቋሚ ኮሚቴዎች የልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ይዞ ወደ ወረዳዎች በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ባለድርሻ አካላት በተገቢ ሁኔታ እየደገፉ እንዳልሆነ የገለጹት አፈ ጉባኤዋ የሕዝብ ሉዓላዊ ምክር ቤቱን ተልዕኮ ተቀብሎ አለማስተናገድ የሚያስጠይቅ መሆኑን በመረዳት የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ከድርጊቱ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የመስኖ ልማት በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ መሥራት እንዲቻል የግብዓት አቅርቦት ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የመማሪያ መጽሐፍት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ሕብረተሰብን ባሳተፈ መልኩ እንቅስቀሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ማቴዎስ ገለጻ በጤናው ዘርፍ የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት ቢፈጸሙም በመድኃኒት ዕጥረትና መሰል ምክንያቶች ዕቅዱ ግብ ሊመታ አልቻለም።

ከ2000 ዓ/ም ጀምሮ እየተንከባለለ የመጣውን የኦዲት ግኝት ከማስመለስ አኳያ ግብረ ሀይል በማቋቋም ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰዋል።

ከገቢ አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪ የገቢ ማጭበርበርንና መሰወርን ለማስቀረት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የፍትህ ተቋማት ቀልጣፋና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ማቴዎስ ከሰላምና ፀጥታ አንጻርም ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።

የምክር ቤቱ አባለት በበኩላቸው በዋና አስተዳዳሪው የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጠንካራና ደካማ ጎኖች ዙርያ በስፋት ተወያይተዋል።

በውይይቱም  የዞኑ መንግስት በምክር ቤቱ የሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለቅሞ በመያዝ እንዲመልስ ጠይቀዋል።

ከአፈር ማዳበሪያ፣ ከግብርና፣ ከትምህርት እና ከጤና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ከመንገድ፣ ከሀዲያ ባሕል ማዕከል ግንባታ እና ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ መስተጋጎልን ጨምሮ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ከምክር ቤቱ አባለት በስፋት የተነሳ ሲሆን የአስፈጻሚ ተቋማት ሀላፊዎችና የዞኑ አስተዳዳሪ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ጉበኤ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል።

ዘጋቢ:- ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን