“የሰው እጅ ከማየት ይልቅ ሰርቼ መኖርን መርጫለሁ” – ተመስገን ደሳለኝ
በደረሰ አስፋው
የአካል ጉዳቱ በሁለት እግሮቹ ላይ የደረሰ ነው፡፡ በልጅነቱ ወድቆ የተከሰተ መሆኑንም ያነሳል፡፡ ሁለቱ እግሮቹ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ የመንቀሳቀሻ ዊልቸር ቢኖረውም አቀበት ቁልቁለቱን መውጣትና መውረዱንም አልቻለም፡፡ ከዚያ ይልቅ በእንብርክክ መሄዱን መርጧል፡፡
በስራ ቦታው ላይ በጠዋቱ ነው የተሰየመው፡፡ በተቀጣጠርነው ቦታ ቀድሜ ብደርስም እሱም የቀጠሯችንን ሰዓት አላዛነፈም፡፡ የእሱን መምጣት በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩ አላፊ መንገደኞችና የመንግስት ሰራተኞች ቁጥርም በዛ፡፡
እኔም ውድ የስራ ጊዜውን ለመሻማት አልቸኮልኩም፡፡ ብቸኛ የገቢ ምንጩ በመሆኑ፡፡ ይልቁንስ የእረፍት ጊዜውን እንድጠብቅ አስገደደኝ፡፡ ቢሆንም ስራውን እመለከት ነበር፡፡ እግሮቹ ተያዙ እንጂ የሰላ አእምሮውና እጆቹ ለስራ ቀልጣፋ ናቸው፡፡
ወጣት ተመስገን ደሳለኝ ይባላል፡፡ የተወለደው በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሀዘንባራ ቀበሌ ልዩ ስሙ ግድራ በሚባል ቦታ ነው። አሁን ነዋሪነቱ በሙዱላ ከተማ ቀበሌ 03 ነው፡፡ አብዛኛው ኑሮውም በዚሁ እንደሆነም ገልጾልናል፡፡
የተሻለ ኑሮን በመሻት ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዱላ ከተማ እንደመጣ ነግሮኛል፡፡ ሀሳቡም ሳይከፋ ትምህርት ቤት ገብቶ የህይወቱን መሰረት እንዲጥልበት አስችሎታል፡፡ ይህን በተወለደበት የገጠር መንደር ሊያገኘው እንደማይችል በመጠቆም፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም በቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሮ እስከ 7ኛ ክፍል ተምሯል፡፡
አሁን ላይ በጫማ ማሳመር (ሊስትሮ) ስራ ላይ ነው የተሰማራው፡፡ ያነጋገርኩትም በዚሁ ስራ ላይ እያለ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አለሁልህ ብሎ ስንቅ የሚሰጠው አልነበረም፡፡ ቤተሰቦቹም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ይኖሩ ስለነበር፡፡ በዚህም ወደ ዘመድ ተጠግቶ መማርን መረጠ፡፡ ይህም ቢሆን የሰመረለት አልነበረም፡፡ በዘመድ ቤት በጥገኝነት የቆየባቸው ስሜቱን የጎዱ ሆኑ፡፡ በዚህም በሰው ቤት ውስጥ ስራ የተወሰነ ጊዜውን እንዳሳለፈ ያስታውሳል፡፡
በሙዱላ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ቤት አቅሙ በፈቀደው ልክ ስራ መስራት ጀመረ፡፡ አብዛኛው ስራ የመላላክ እንደነበርም ነው የተናገረው፡፡ የሆቴል ቤቱ ባለቤትም እሱን ለመደገፍ እንጂ በውል ስራን እንዲያግዘው አልቀጠረውም፡፡ በዚህ ሆቴል ለ3 ወራት ከሰራ በኋላ 800 ብር አገኘ፡፡ በዚች ብር እራሱን የሚለውጥበት መላ አበጀ፡፡
ከሰው ቤት ይልቅ የራሱን ስራ ፈጥሮ ለመስራት ወሰነ፡፡ ከሚበላውና ከሚጠጣው ቆጥቦ የሊስትሮ እቃዎችን ማለትም፡- ቀለምና ብሩሽ ገዝቶ ወደ ስራ ገባ፡፡ በዚህ የጫማ ማሳመር ስራ አምስት ዓመታትን አሳልፏል፡፡ የሊስትሮ ስራ እየሰራ 7ኛ ክፍል ላይ ያቆመውን ትምህርቱን እስከ 10ኛ ክፍል ለመማር ቻለ፡፡
10ኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላም ትምህርት በቃኝ አላለም፡፡ በሙዱላ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ገብቶ በኮንስትራክሽን ሙያ በዲፕሎማ ተመረቀ፡፡ ከተመረቀም 3 ዓመታት መቆየቱን ያነሳል። ይሁን እንጂ በተማረበት ሙያ የስራ ዕድል ማግኘት አልቻለም፡፡ የሊስትሮ ስራውን ግን እንደቀጠለ ነው፡፡
አሁን ህይወቱን የሚመራው በሊስትሮ ስራ ነው፡፡ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማህበር ባዘጋጀለት የመስሪያ ሼድ የጫማ ማሳመር ስራን ይሰራል፡፡ ይህም የህይወቱ አንድ እርምጃ እንደሆነ ያነሳል። በገጠር እና በከተማ በቤት ተደብቀው ከሚገኙት በተለየ ወጥቶ መስራት መቻሉን እንደ እድል ይቆጥረዋል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው እንዲከበር ባቋቋሙት ማህበር የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ አካል ጉዳተኞች ማህበርን በፀሀፊነት ያገለግላል። አካል ጉዳተኞች በማህበር ተደራጅተው መንቀሳቀሳቸውም መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር እንደሚያግዝ ይናገራል፡፡
“ዊማ” የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅትም አካል ጉዳተኞች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው እንዲጎለብት ለማድረግ የሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠናም እንዳገዘው ተናግሯል፡፡ ስራን እንዴት መፍጠር እንደሚቻልና የገንዘብ አጠቃቀምን በተመለከተ ስልጠናዎቹ አጋዥ ናቸው፡፡ ድርጅቱ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ አራት ሼድ አዘጋጅቶ የሰጠ ሲሆን ከዚህም ወጣት ተመስገን አንዱ ተጠቀሚ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡ ይህም ከጸሀይና ከዝናብ እንደታደገውና ስራውን በተገቢው ለመከወን እንዳገዘውም ገልጿል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ገብቶ ሲማርም የጫማ ማሳመር ስራው የገቢ ምንጩ ነበር፡፡ የወጪ መጋራት ክፍያንም ከፍሏል፡፡
ከጉልበት በታች ሁለቱም እግሮቹ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ሌላ አማራጭ ስራዎችን እንኳ ለመስራት የሚያስችለው አቅም የለውም፡፡ ወደፊት ቢሳካለት ደግሞ ሱቅ አለያም የጫማ ማደሻ ለመክፈት ዕቅድ አለው፡፡ ለዚህም ድጋፍ የሚያደርግለትን ግለሰብ አለያም ድርጅት ድጋፍን ለማግኘት ይሻል፡፡
ወጣት ተመስገን ዛሬ ላይ በሊስትሮ ስራ የችግረኛ ቤተሰቦቹ ረዳት ነው፡፡ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቹ ካለው የመሬት ጥበት የተነሳ የሚያመርቷትም ቢሆን ከ2 ወር የዘለለ እንደማያሻግራቸው ይናገራል፡፡ ይህም የእሱን እጅ እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸው ነው የሚገልጸው፡፡ ይህ ግን እሱን አላስከፋውም። ደስተኛ አደረገው እንጂ፡፡ ሰርቶ ከራሱ አልፎ የቤተሰቡ ደጋፊ በመሆኑ ደስታው ጥልቅ ነው፡፡
በርካታ አካል ጉዳተኞች እየለመኑ ሲያይ ይቆጨዋል፡፡ አካል ጉዳተኛ ለልመና የተፈጠረ አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንም የአስተሳሰብ ድህነት አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ “አካል ጉዳተኝነት ስራን ፈጥሮ ከመስራትና ሀብት ከማፍራት የሚገድብ አይደለም፡፡ ሰርቶ ለሌሎችም መትረፍ ይቻላል፡፡ አካል ጉዳት የድህነት ምክንያት ሊሆን አይችልም” ሲል ይሞግታል፡፡
“እኔ የሰውን እጅ ከማየት ይልቅ ሰርቼ መኖርን መርጫለሁ፡፡ ከፈጣሪ ጋር የሚቻለኝን አደርጋለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ በመስራቴ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለማንቃት ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ተሞክሮዬን በማጋራት እራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዳይመለከቱ የማንቂያ ደውል ነው የሆንኩት፡፡
“አካል ጉዳተኞች በአንድ ጥላ ስር መሰባሰባችን ይህንን እውቀቴንና አመለካከቴን ለሌሎች ለማሳወቅ እድል ፈጥሮልኛል፡፡ አካል ጉዳተኞች ተስፋ ያላቸው እንጂ ተስፋ እንደሌላቸው አድርገው የሚመለከቱት ትክክል አይደለም፡፡
“በሰለጠንኩበት የሙያ ዘርፍ የመንግስት ስራ ተቀጣሪ ለመሆን ብዙ ጠብቄያለሁ። ግን አልሆነም፡፡ በዚህ ግን ተዘናግቼ አልተቀመጥኩም፡፡ ሌላውን አማራጭ ቃኘሁ፡፡ የሊስትሮ ስራም ካለኝ አቅም አኳያ ተመራጭ ሆነልኝ፡፡ በዚህ ስራ እራሴን አስተዳደርኩ፣ ተማርኩበት፣ ቤተሰብንም ረዳሁ፡፡ ወደፊትም በላቀ የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ነው እቅዴ” ሲል ነው የገለጸው።
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው