በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በግብርና ስራ በተለይም በጓሮ አትክልት፣ በአዝርእትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በ2016 በጀት ዓመት በ6 ወራት ውስጥ ለ1ሺህ 225 ወጣቶች በቋሚና በጊዚያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ስራ ዕድልና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።
በጋሞ ዞን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ለአትክልት፣ ፍራፍሬና አዝዕርት ምርት እጅግ ተስማሚ ስነ ምህዳር ስላለው በርካታ ወጣቶች በዘርፉ ተሰማርተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው ተመልክቷል።
በወረዳው በዘርፉ ከተሰማሩ ኢንተርኘራይዞች መካከል በላንቴ ቀበሌ የሚገኘው ኑይሳ የጓሮ አትክልትና አዝዕርት ችግኝ ማባዣ ማህበር ተጠቃሽ ሲሆን፥ በአነስተኛ ቦታ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በስፋት በማባዛት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ወንድማገኝ መስፍን በአነስተኛ ቦታ አፕልን ጨምሮ ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ሙዝ፣ ሀባብና የተለያዩ ችግኞችን በማፍላት ከአከባቢያቸው አልፈው እስከ ተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እንደሚልኩ ተናግሯል።
ማህበሩ ስራውን በማስፋት ለበርካታ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች ስራ ለመፍጠር ዝግጅት ቢያደርግም የቦታ እጥረት እንደገጠመው ወጣት ወንድማገኝ አስረድቷል።
ወጣቱ ስራን ሰርቶ መለወጥ እንደሚችል ማህበራችን ማሳያ ነው ያለችው ደግሞ የማህበሩ አባል ወጣት ፅገሬዳ መስፍን ስትሆን በምህንድስና ብትመረቅም የመንግስትን ስራ ከመጠበቅ ወደ ግብርናው ስራ መሰማራቷን ተናግራለች ።
ማህበሩ ከራሱ አልፎ ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች በተለይም ለሴቶች ስራ መፍጠሩን የሚናገሩት ደግሞ የግብርና ባለሞያው አቶ በላይነህ ብሴና አቶ መስፍን መኩሪያ ሲሆኑ ወጣቱ በዙሪያው ያለውን ምንዳ ማማተርና መስራት እንዳለበት መክረዋል ።
የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መርደኪዮስ ኬርባ ለማህበሩ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ከማመቻቸት ባለፈ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልፀዋል ።
የአርባምንጭ ወረዳው ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ሙልአቶ በወረዳው በ6 ወራት ውስጥ ለ1ሺህ 225 ወጣቶች ስራ መፈጠሩን ጠቁመዋል ።
ለኑይሳ የጓሮ አትክልትና አዝዕርት ችግኝ ማባዣ ማህበር ለጊዜው 1 ሺህ ካሬ መሰጠቱንና በቂ አለመሆኑን ተናግረው በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቂ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ከችግኝ ብዜት ባሻገር የአረንጓዴ ልማት መርሀ ግብርና በበጋ ስንዴ ልማት የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል ኃላፊዎቹ ።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ