ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ ለተከታታይ 15 ቀናት ሲካሄድ የቆየው ልዩ ልዩ የበጋ ስፖርት ሻምፕዮና ውድድር ተጠናቀቀ።
በተጠናቀቀው የበጋ ሰፖርት ሻምፕዮና በታዳጊዎችና አዋቂዎች የእግር ኳስ ጨዋታ፣ ሩጫ እና ገመድ ጉተታ ለዋንጫና ለወዳጅነት ሲካሄድ ቆይቷል።
የውድድሩ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የኬሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ኃይሉ ተወዳዳሪዎችና የስፖርቱ ማህበረሰብ ያሳዩትን ትጋት አድንቀው ለቀጣይ ክረምት ስፖርት መርሐግብር ሜዳውን ከማስዋብ አንስቶ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ነው የገለጹት።
የኬሌ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አማረ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የስፖርት ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የታየበት፣ ከተማንና ዞኑን የሚያስጠሩ ተወዳዳሪዎች የተለዩበትና የስፖርታዊ ጨዋነት የታየበት የስፖርት ሻምፒዮና እንደነበር ተናግረዋል።
ለዋንጫ ጫዋታ ከታዳጊዎች መቀሬዲ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት 5ለ 4 በሆነ ውጤት፣ ኬሌ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤትን በማሸነፍ፣ በአዋቂዎች ጤና ዋርካን 1ለ 0 በማሸነፍ ጨዋታው ተጠናቋል።
በመጨረሻም የኬሌ ከተማ አስተዳደር፣ የሁለቱም ወረዳና የዞን አመራሮች በተገኙበት ከተለያዩ ቡድኖች የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት ላሳዩና ውጤት ላስመዘገቡት የናስ፣ የብርና የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማን በመርታት ወደ አሸናፊነት ተመለሰ
በ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ በንቃት በመሳተፍ የሚፈልገውን መንግስት ለመምረጥ መዘጋጀት እንዳለበት ተገለጸ
ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው – አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል