በቀቤና ልዩ ወረዳ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ማህበራት ልዩ ወረዳው በሚያደርግላቸው ድጋፍና ክትትል ውጤታማ እየሆኑ ነው

ሀዋሳ፡ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴደ) በቀቤና ልዩ ወረዳ በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ማህበራት ልዩ ወረዳው በሚያደርግላቸው ድጋፍና ክትትል ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገለፁ።

በተያዘው በ2016 በጀት ዓመት በባለፉት 7 ወራት ውስጥ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ 96 ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ መሰማራታቸውን የልዩ ወረዳው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራዝ ልማት ፅ/ቤት አስታውቋል።

በልዩ ወረዳው ካሉ ውጤታማ ከሆኑ ማህበራት መካከል በ 2009 ዓ/ም በ5 አባላትና በ50 ሺህ ብር ካፒታል ወደ ስራ የገባው ተወከል የቤትና የቢሮ እቃዎች አምራች ማህበር አንዱ ነው።

በ50 ሺህ ብር ስራ የጀመረው ማህበሩ አሁን ላይ ካፒታሉ ከ4 ሚልዮን ብር በላይ መሆኑን ነው የማህበሩ ሊቀመንበር መሃመድ ነጋሽ የገለፀው።

ማህበሩ ከአባላቱ ባለፈ በጊዜያዊና በቋሚነት ለብዙ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉም ነው ሊቀመንበሩ መሃመድ የነገሩን።

ለዚህ ውጤታማነትም የልዩ ወረዳው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ፅ/ቤት ድጋፍና ክትትል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገላቸው የገለፁት ሊቀመንበሩ ማህበሩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የማምረቻና መሸጫ ቦታ ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባም አክለዋል።

ማህበሩ ውጤታማ በመሆኑ ከክልል ተቋማት ጭምር  የተለያዩ ስራዎችን ትዕዛዝ በመውስድ እየሰራ እንደ ሚገኝ ገልፀዋል።

ወጣት ቸርነት እንየው የማህበሩ አባል ሲሆን ከዚያ ቀደም በግሉ ይሰራ እንደነበር አስታውሶ ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ ከአባላቱ ጋር በመነጋገር ማህበር እንደመሰረቱ ተናግሯል።

በዚህም ውጤታማ መሆን መቻላቸውንና አሁን ላይ ወንድሞቹንም ከፍሎ እያስተማረ እንዳለም ተናግሯል።

ወጣት እዮብ አሸብር ደግሞ በማህበሩ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሲሆን የማህበሩ ውጤታማነት ከማህበሩ አባላት ውጭ ላለነው መትረፍ ችላልም ብሏል።

ሌሎች ወጣቶችም የኛን ውጤታማነት በማየት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተደራጅተው ቢሰሩ የሰው እጅ ከማየትና የቤተሰብ ጫና ከመሆን ተላቀው ለሃገርም መትረፍ ይችላሉም ብለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙዴ ሙዘሚል በተያዘው በ2016 በጀት ዓመት በ 7 ወራት ውስጥ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በአገልግሎት ዘርፍ 96 ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ መሰማራታቸውን ገልፀዋል። በዚህም ለ5 መቶ 57 በጊዜያዊና ለ7 መቶ 96 ወጣቶች ደግሞ በቋሚነት በድምሩ ለ1ሺህ 353 ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት አንፃር የሚታዩ ጉድለቶችን ለመሙላት 20 በ80 ልማት ባንክ ለሚገነባው ሼድ የካርታ ፕላን በማስያዝም ተግባሩ በሂደት ላይ መሆኑንም የጽ/ቤቱ ኃላፊ ገልፀዋል።

በአመቱ ለማስቆጠብ ከታቀደው 6 ሚልዮን በ7 ወራት ውስጥ 3 ሚልዮን 1መቶ 53 ሺህ ብር ማስቆጠብ ተችሏል ነው ያሉት አቶ ሙዴ።

4 ሚልዮን 411ሺህ 671 ብድር ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ 1ሚልዮን 950 ሺህ ብር መሰራጨቱን ነው የገለፁት ኃላፊው።

ቀጣይ ሌሎች ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ብድር የወሰዱ ማህበራት ብድሩን በወቅቱ መመለስ እንዳለባቸው አስታውሰው ለዚህም ብድር ለማስመለስ የተቋቋመው ግብረ ሃይል በትኩረት እንዲንቀሳቀስ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደተግባር መገባቱን አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጠቢያችን