የዜጎችን ተጠቃሚነትና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ፓርቲው የገባውን ቃልና ያስቀመጠውን ራዕይ ዕውን ያደርጋል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

የዜጎችን ተጠቃሚነትና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ፓርቲው የገባውን ቃልና ያስቀመጠውን ራዕይ ዕውን ያደርጋል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በቀሪ አጋማሽ የምርጫ ዘመን የዜጎችን ተጠቃሚነትና ብልፅግናን እውን እንደሚያደርግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

“ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ የአመራርና የአባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በቀሪ የምርጫ ዘመን የዜጎችን ተጠቃሚነትና ብልፅግናን እውን በማድረግ ቅቡልነቱ የተረጋገጠ ፓርቲ፣ ብቃት ያለዉ መንግስትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ብለዋል።

እንደ ሀገርና ክልል የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል ቀይረን ተሻግረናቸዋል ያሉት አቶ ጥላሁን፥ ለዘመናት የነበሩ አገራዊ ስብራቶች በነበረን ቁመና መፍታት እንደማንችል መረጋገጡ፥ ሀገራዊ ለውጥ እንዲካሔድ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር በተለወጠ ዓለም ውስጥ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ስንለወጥ ብቻ መሆኑ ፓርቲው በደረሠበት ስምምነት መሠረት ብልፅግና ሰዉ ተኮር፣ ሀገር-በቀል የፖለቲካ እሳቤ የሚከተል፣ የመሃል ፖለቲካ አራማጅ፣ ‘ፕራግማቲክ’፣ ሚዛን ጠባቂ፣ አፍርሶ የማይጀምር፣ ጊዜን ያስተሳሰረና መደመርን የብልፅግና መዳረሻ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ለዚህም ፓርቲው በአዲስ ክልልና በአዲስ እሳቤ የደቡብ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የብልፅግናና የመቻቻል ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና እንዲሁም በልማትና መልካም አስተዳደር ስብራቶች ላይ የበለጠ ለመስራት የአመራርና የአባላት ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን  አስረድተዋል።

በቀሪው የምርጫ ዘመን ቅቡልነቱ የተረጋገጠ ፓርቲ፣ ብቃት ያለዉ መንግስትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የበለጠ እንደሚሰራ ጠቁመዉ፥ የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ