የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት የአጋማሽ ምርጫ ዘመን ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገለጸ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት የአጋማሽ ምርጫ ዘመን ስኬታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገለጸ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በአጋማሽ የምርጫ ዘመን ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ገለጹ።

ፓርቲው የአመራርና የአባላት ማጠቃለያ ኮንፈረንስ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ነው።

በኮንፈረሱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ፥ በአጋማሽ የምርጫ ዘመን ያከናወናቸውን ተግባራት መነሻ በማድረግ፥ ስኬቶችና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዕውን እንዲሆኑ ለማስቻል፥ ጉድለቶችን በቁጭት አቅዶ ለመስራት ከመላው አመራሩና አባላት ጋር የጋራ መግባባትና ግንዛቤ መያዝ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች በዋናነት የፓርቲውን መሠረታዊ ምሰሶዎች ላይ የጋራ ተግባቦት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ ሀገረ-መንግስት  ግንባታ ላይ ያስመዘገብነው ስኬት ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ፥ ተቋማዊ መሠረት ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲያብብ የተጫወትነው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል። 

እርቀሠላም በማውረድ ክልላዊ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሠላምን ለመገንባት የተሠራው ስራም ከፍተኛ በመሆኑ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በዚህ ላይ የጋራ ግንዛቤ ሊይዙ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከምግብ ዋስትና ጥያቄ የተሻገረ የበለጸገ ኢኮኖሚ ለመገንባት በተያዘው እርብርብ ውጤት የመጣበት መሆኑን ጠቁመው፥ የህዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላ ፍትሐዊ የማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት የተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የመጣንበት መንገድ ስኬት ብቻ አልነበረም ያሉት ኃላፊው፥ ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ከአደረጃጀትና ከአስተዳደር ወሰን ጋር የነበሩ ችግሮች የለውጡ ተግዳሮት እንደነበረ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጓዳኝ፥ ከዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ጥቅም ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች የክልሉን ብልጽግና በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ እንዳደረገው አንስተዋል።

የክልሉ የገቢ አሠባሰብ ውስንነት፣ የአመራሩ የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም ዝቅተኛ መሆን፣ ሀገር አቀፍና ዓለማቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የብልጽግናችን ፈታነዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በቀረበውና በሌሎችም ጉባኤው በሚመክርባቸው የአጋማሽ ምርጫ ዘመን አፈጻጸም ላይ በስፋት እንዲመክሩበት ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ