ሴቶችን በሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማብቃት የሁሉም አካል ርብርብ አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ

ሴቶችን በሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማብቃት የሁሉም አካል ርብርብ አስፈላጊ መሆኑ ተገለፀ

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት “ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትንና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ የሴቶችን አቅም በማጎልበት ፊት ያሉ አመራር ሴቶችን ፈለግ በመከተል ብቁና አገሪቱን መምራትና በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ሴቶች ለሁሉም አርዓያ በመሆን በሀብት፣ በእውቀትና በመልካም ስነምግባር የታነፁ፤ በመሪነት የተመሰከረላቸው እየሆኑ መምጣታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሁሉም ርብርብና ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የይርጋጨፌ ሴቶችና ህፃናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ደንቢ፤ ሴቶችን በሁለንተናዊ ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ አደረጃጃት በማቋቋም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ብቁ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ሴቶች ቁጠባን እንዲለማመዱ፣ በግብርና ዘርፍ በንቃት እንዲሳተፉና በአመራር ዘርፍም በብቃት እንዲመሩ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ለሰባት መቶ ሴቶች በገቢ ማስገኛ መስኮች ላይ ስልጠና በመስጠት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሼዶችን በማዘጋጀት ከኦሞ ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተው መድረኩ ሴቶችን በማነቃቃት በሁሉም ረገድ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል ወ/ሮ ነፃነት ተስፋዬና ወ/ሮ እመኙ ወንድፍራው እንደተናገሩት ይርጋጨፌ ከተማ ሴቶችን በትምህርት፣ በቁጠባ፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች ለማብቃት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን በማንሳት በሀገር ደረጃ በትምህርት፣ በግብርናና በሌሎች ያሉብንን ስብራቶች ከመጠገን ረገድ ሴቶች ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆኑ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መድረኩ የጎላ ጠቀሜታ አለው፡፡

ሴቶች የወንዶችን እጅ ከመጠበቅ በሥራና በአመራር ፊት የወጡ ሴቶችን ፈለግ በመከተል በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ፡፡

በመድረኩም ለአቅመ ደካሞች የዱቄት፣ ዘይትና ሳሙና አልባሳት ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው ለቆሙ ድርጅቶችና ጽ/ቤትም የምስክር ወርቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዘጋቢ: ዮሴፍ ቶልኬ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን