ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን  ለመከላከል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በብቃት ለመምራት  የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ

ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን  ለመከላከል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በብቃት ለመምራት  የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን  ለመከላከል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በብቃት ለመምራት  የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከልማት ድርጅቶች እና ከህዝባዊ ድርጅቶች ለተወጣጡ 900 ለሚደርሱ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ  ሥራ አስፈጻሚዎች በኮሚሽኑ የአሠራርና የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ  ለአምስት ተከታታይ ቀናት  የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው የተሳተፉ የሥነ-ምግባር መከታተያ  ሥራ አስፈጻሚዎች በበኩላቸው የትብብርና የቅንጅት መላላት የዘርፉን ውጤታማነት እየተፈታተነው  እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሙስናንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል በሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተቋማት አመራሮች ቁርጠኝነት  አነስተኛ መሆኑንም የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎቹ ተናግረዋል።

በፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥነ-ምግባር ግንባታና የሙስና መከለከል ሥልጣና መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀረጎት አብርሃ በበኩላቸው  በፌዴራል ተቋማት ብቻ 1146 የሚደርሱ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ኦፊሰሮች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከእነዚህ መካከል 900 ለሚደርሱ ኦፍሰሮች የተሰጠው ሥልጠና የፀረ-ሙስና ትግሉን ለማጠናከር አቅም እንዲገነቡ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በተለይም በኮሚሽኑ የህግና የአሠራር ማዕቀፎች ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ በመጨበጥ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት  መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ሀረጓት አስገንዝበዋል።

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በበኩላቸው፤  የፀረ ሙስና ትግሉን ህዝባዊ መሠረት በማስያዝ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያግዙ የህግና የአሠራር ማዕቀፎች የተዘረጉ ቢሆንም በዘርፉ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት  የሁሉንም ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።

ብልሹ አሠራሮችን ፈጥኖ ለመቅረፍ የሚያግዙ የአሠራር ስልቶችን በመጠቆም ረገድ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ክፍሎች የላቀ ድርሻ እንዳለቸው ምክትል ኮሚሽነሩ  አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሴክተሮች  ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ /ሮ አልማዝ መሰለ በስልጠናው ማጠቃለያ ለይ ተገኝተው  ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሌብነትንና ብልሹ አሠራሮች በመከላከል የህዝብና የመንግሥት ሀብት ከምዝበራ  እንዲጠበቅ ለማድረግ በመንግሥት  በኩል ቁርጠኛ አቋም መያዙን  ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በየደረጃው ባሉት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ  የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ክፍሎች ራሳቸውን በሥነ-ምግባር በማነጽ ሌሎችን ለማነጽ ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአደማ ከተማ ስሰጥ  የነበረው  የ25ቱ ዘርፎችና የተጠሪ ተቋማት የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ክፍሎች ሥልጠና  ተሳታፊዎች የአቋም መግለጫ በማውጣት ሥልጠናውን አጠናቀዋል።

ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ