ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት ተግተው እየሰሩ መሆኑን በገዋታ ወረዳ ህንጊዶ ቀበሌ የሚገኘው አላየው መላኩ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ክለብ ሰልጣኝ ታዳጊ አትሌቶች ተናገሩ

ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት ተግተው እየሰሩ መሆኑን በገዋታ ወረዳ ህንጊዶ ቀበሌ የሚገኘው አላየው መላኩ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ክለብ ሰልጣኝ ታዳጊ አትሌቶች ተናገሩ

የሚመለከታቸው አካላት ስንቅና ሞራል እንዲሆኗቸውም ጠይቀዋል፡፡

የሃምሳ አለቃ አላየው መላኩ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ክለብ በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ በግል ባለሀብቱ አላየው መላኩ ተነሳሽነትና መስራችነት በ2015 ዓመተ ምህረት 38 ሰልጣኞችን በማቀፍ የተቋቋመ ነው፡፡

በተግባርና ንድፈ ሀሳብ እየወሰዱ ያሉት ስልጠና ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ከክለቡ ሰልጣኝ አትሌቶች መካከል አንዳንዶቹ በቀጣይ ጠንክረው በመስራት ሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ለማስጠራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ ሀገር አቀፍና ክልላዊ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ መቅሰማቸውን የገለጹት ታዳጊ ሰልጣኝ አትሌቶቹ፤ ቀጣይነት ባለው የውድድር መድረክ መሳተፍ እንዲችሉ ዕድሉ ሊመቻች እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ የስልጠና ቁሳቁሶች ታግዘው እንደሚሰለጥኑ ጠቁመው የሚመለከታቸው አካላት ሞራልና ስንቅ እንዲሆኗቸው ጠይቀዋል፡፡

የክለቡ አሰልጣኝ አሳየ አትርሳው ታዳጊ ሰልጣኝ አትሌቶች 38 መሆናቸውን አስረድተው የሚሰጣቸውን ትምህርት የመቀበል ፍላጎትና ዝንባሌአቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የህንጊዶ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ መኩሪያ በበኩላቸው የግል ባለሀብቱ ቀጣይ ትውልድ ላይ መስራቱ ለሌሎች አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል፡፡

ወጣት ባለሀብቱ እያደረገ ያለው ተግባር ሊበረታታ ይገባል ያሉት የወረዳው ዋና አሰተዳዳሪ አቶ አርጋው ሀይሌ፤ ለወጣቶቹ የመለማመጃ ሜዳን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ እንቅሰቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ወጣቶቹም ሊያዘናጋቸው ከሚችሉ ተግባራት ሊርቁ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ የሺዋስ ዓለሙ፤ የግል ባለሀብቱ ታዳጊ ወጣቶች በዘርፉ ሀገሪቱን በዓለም አደባባይ እንዲወክሉ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑንና ለሌሎች አርአያነት ያለው እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ክለቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን በሚያዘጋጃቸው ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸው በቀጣይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን