የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እና ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በጋራ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ህገ ወጥነትን ለመከላከል እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ያለመ ውይይት ከባለሀብቶች ጋር በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል።
ባለሀብቶች በመንግሥት መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮችን በዝርዝር አንስተዋል።
የንግዱን ዘርፍ ጤንነት ለመጠበቅ ሰላምን መጠበቅ መተኪያ የለውም ያሉት ባለሀብቶች የክልል መንግሥትታት ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ በክልሉ አለመኖር፣ ለዱቄት ፋብሪካዎች የስንዴ ግብዓት በበቂ መጠን አለመኖር፣ የንግድ መተዳደሪያ ህጎች ላይ የንግዱ ማህበረሰብ ዕውቀት አናሳ መሆን፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ቢሮክራሲው የተንዛዛ መሆን፣ የገበያ ትስስር ዕጥረት፣ ተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ፣ የባንክ ቤት ብድሮችና በመንግሥት ድጎማዎች ላይ የፍትሐዊነት መጓደል መስተካከል እና መቀረፍ አለበት ብለዋል።
ኑሮ ውድነት እና ህገ ወጥ ንግድ ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው በመሆኑ ህገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ በጋራ መስራት አለብን በማለት አንስተዋል።
ፍላጎት እና አቅርቦትን ማጣጣም፣ የውሃ፣ መብራት እንዲሁም የመንገድ መሠረተ ልማት ክፍተቶች በጋራ ጥረት መሻሻል አለባቸው ብለዋል።
ከተሳታፊዎች ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች መልስና ማብራሪያ ተሰጥተዋል።
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው፤ ህግ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለው በቀጣይ አጥፊዎች ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ገልጸዋል።
በክልሉ የተሻለ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቅርንጫፍ በክልሉ ለመክፈት እየሰራን ነው ብለዋል።
የስኳር እና የዘይት ምርት አቅርቦት ችግር በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ ነገር ግን ወጥ የዋጋ ተመን አለመኖሩ ተመላክቷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል በበኩላቸው ህገ ወጥነት ህጋዊ ስርዓትን የመናድ አቅም ያለው በመሆኑ በጋራ መከላከል የሁሉም ዜጋ ድርሻ ነው ብለዋል።
ሽያጭን በደረሰኝ የማድረግ ባህል እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ያሉት አቶ ስንታየሁ ይሄ ተግባር በጊዜ መታረም አለበት በማለት ተናግረዋል።
በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚስተዋሉ የተንዛዙ አሰራሮች እና ሌብነቶችን ለመቅረፍ መንግሥት ይሰራል።
የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ደግሞ ግብር እና ለኢንዱስትሪ ልዩ ትኩረት በመስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
የግል ባለሀብቱ ከራሱም በማለፍ ለሀገር እና ለመላው ዜጋ በተለይም ለተቸገሩ ወገኖች የመትረፍ ባህል እንዲያዳብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የመብራት መቆራረጥ እየተፈጠረ ያለው በሀይል አቅርቦት እጥረት ሳይሆን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች መድከም በመሆኑ መስመሮቹን ለመተካት ስራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ክልሉን ሰላማዊ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው ሰላምን ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎችም ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በባህላዊ ስርዓቶች እየተፈቱ ነው ብለዋል።
ምርትና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ በስፋት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
ህገ ወጥ ተግባርን መንግሥት እንደማይታገስና የንግዱ ማህበረሰብም ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አሁን ላይ ሰላምን ለማስጠበቅ፣ ለግብርናና ለትምህርት ዘርፍ፣ ለጤና ብሎም የንግዱን ዘርፍ ለማዘመን በትጋት እና በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ