በደቡብ ኦሞ ዞን አገራዊ ምክክር ለአገራዊ መግባባት በሚል መርህ ሲካሄድ የቆየው የየማህበረሰብ ተወካዮች ምርጫ መጠናቀቁን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ

በደቡብ ኦሞ ዞን አገራዊ ምክክር ለአገራዊ መግባባት በሚል መርህ ሲካሄድ የቆየው የየማህበረሰብ ተወካዮች ምርጫ መጠናቀቁን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ

በማጠቃለያው መርሃግብር በዞኑ በ3 ወረዳዎች የሚኖሩ ማህበረሰብ ክፍሎች በኮሚሽኑ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን ምርጫ አካሂደዋል።

በዞኑ ቱርሚ ከተማ ለሁለት ተከታይ ቀናት ሲካሄድ በቆየው የየማህበረሰብ ተወካዮች ምርጫ ሂደት ማጠቃለያን በተመለከተ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደገለፁት የሀገራዊ ምክክር ዋነኛ ግብ እንደአገር ያልተግባባንባቸዉን መሠረታዊ ጉዳዮችን በመለየት፣ መንስኤዎቻቸዉን ነቅሶ በማዉጣት በመነጋገርና በመመካከር የጋራ መግባባት መፍጠር የሚቻልበት ሂደት ነዉ።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካና የሐሳብ መሪዎች እንዲሁም ከአገር ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ተዉልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ስለአገሩ በሚደረገው ምክክር በዉክልና ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል።

ኮሚሽነሩ አያይዘዉም አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመገንባት በሂደትም የመተማመንና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበትና የተሸረሸሩ ማህበራዊ እሴቶችን ለማደስ እንደሚጠቅም ይታመንበታል ብለዋል።

አገራዊ ምክክር ከሌሎች ግጭት መፍቻ መንገዶች በተለየ መልኩ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ መስማማት ላይ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ለሆኑ እና መተማመንን ለሚፈጥሩ መግባባቶች መደላድል የሚያበጅ እንደሆነም ኮሚሽነሩ አሰረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን