የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉንም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ሴቶች ገለጹ

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉንም ርብርብና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ሴቶች ገለጹ

በዞኑ የሚስተዋለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት ተጨባጭ ተግባራት እየተከናወኑ እንዳለም ተመላክቷል።

በብዙ መሠናክልና ጥረት በአከባቢው ያለውን ተጽእኖ ተቋቁመው ለከፍተኛ ትምህርት የደረሱት የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎቹ ወጣት ሜሮን ረቴና ሻጋ አሎ፤ አርብቶ አደር መሆን ከትምህርት እንደማያግድ አውስተው የህይወት ተሞክሯቸው ለሌሎች አስተማሪ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

በአከባቢያቸው ሴቶች ከትምህርት ይልቅ ለትዳር፤ የተሻለ ደረጃ ላይ ከመድረስ ይልቅ በከብት ጥበቃ ስራ መዋላቸው ጎጂ ልማድ ሆኖ መቆየቱን ባለታሪኮቹ አንስተዋል።

ይህን ስር የሰደደ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ ሴቶች ሊግ ኃላፊ ወ/ሮ ናቱክ ሩክሩኖና የወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ካሬ በጋራ በሰጡት አስተያየት በወረዳው አስገድዶ መድፈር፣ ያላቻ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻና በሴቶች ላይ የሚደርስ የስራ ጫና በዋናነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

የሴቷ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ቀዳሚው ትምህርት በመሆኑ በዚህ ረገድ ሰፊ ስራ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

በዞኑ የሳላማጎ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ተረፈች ኢቶ በበኩላቸው በወረዳው በርካታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መኖራቸውን ጠቁመው ይህንንም ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ስራ እየተሰራ በመሆኑ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በዞኑ የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀርፍ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባና በተለይ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለማስቀረት ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የደቡብ ኦሞ ክላስተር ማስተባበርያ ቢሮ ፕሮግራም ማናጀር አቶ አለማየሁ ብርሀኑ በደቡብ ኦሞ ዞን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ለማስቀረት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውንና ችግሩን ለመቅረፍ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን