የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን በመገኘት “ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ቃል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ በመገኘት “ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ቃል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ በማሰባሰብ የሚያቀርቡ ተወካዮች ምርጫን በኮንሶ ዞን 4 ወረዳና 1 ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ማህበረተሰብ ተወካዮች እንደሚያካሂዱም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ የሀገራችን ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን በማስመረጥ ላይ እንዳለ ይታወቃል፡፡
ኮሚሽኑ እስከአሁን ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በሰባት ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳድሮች የተሳካ የተወካዮች መረጣን ማከናወኑን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ገልጸዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ገለጻ ኮሚሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኙ በአስራ ሁለት ዞኖች ከዚህ በፊት ባሰለጣናቸው ከሁሉም የዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር በተወጣጡ ተባባሪ አካላት ታግዞ ከህብረተሰቡ የሚቀርቡትን አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች ልየታን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት ተቋሙ በተባባሪ አካላቱ አስተባባሪነት በህብረተሰቡ የተመረጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በዞኑ በሚገኙ ከአራት ወረዳዎችና ከአንድ ከተማ አስተዳደር ማለትም ከሰገን ዙሪያ፣ ከከና፣ ከኮልሜና ከካራት ዙሪያ ወረዳዎች እንዲሁም ከካራት ከተማ ከተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች መረጣ እንዲከናወን ያደርጋል፡፡
በተወካዮች መረጣው ላይም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን የሚወክሉትም የማህበረሰብ ክፍል ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ እድሮች፣ የመንግስት ሰራተኞችና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ያልቻሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እና እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ተፈናቃዮችን ነው፡፡
መረጣውም አካታችነት፣ ግልጽኝነት፣ አሳታፊነት እና ተዓማኒነትን ያገናዘበ እንዲሆን እንደሚደረግ ነው ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ የገለፁት፡፡
በሂደቱም ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ሁለት ሁለት ተወካዮችን ከአንዳንድ ተጠባባቂ ጋር ይመርጣሉ፡፡
ኮሚሽኑ መላውን የኮንሶ ዞን ነዋሪዎች፣ እንዲሁም ባለድርሻ አካላት የዞኑን አስተዳደር ጨምሮ አጀንዳ በሚሰጡ ተወካዮች መረጣ ሂደት የሚሳተፉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመለየት ሲደረግ በነበረው ስራ ላይ ላሳዩት ትብብር እና ተሳትፎ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ አመስግነዋል፡፡
በነገው ዕለት የሚከናወነውን ከህብረተሰቡ የሚቀርቡትን አጀንዳዎች በማሰባሰብ ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡ ተወካዮች መረጣ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ወገን የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ሂደትም ያለምንም እንከን እንዲፈጸም ህዝቡ እና በዞኑ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጭምር ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ