የጋሞ ዞን የባህል ፌስቲቫልና መላ የስፖርት ሻምፒዮና በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የጋሞ ዞን የባህል ፌስቲቫልና መላ የስፖርት ሻምፒዮና በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ሀዋሳ፡ መጋቢት 03/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጋሞ ዞን የባህል ፌስቲቫልና መላ የስፖርት ሻምፒዮና በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የወንዶች እግር ኳስ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዞን ደረጃ በእግር ኳስ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የስፖርት ዓይነቶችም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አሳስበዋል።

የጋሞ ዞን የባህል ፌስቲቫልና መላ የስፖርት ውድድር የመዝጊያ ሰነ-ስርዓት ሲካሄድ በወንዶች እግር ኳስ ፍፃሜ የተገናኙት የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ እግር ኳስ ቡድንና የብርብር ከተማ አስተዳደር እግር ኳስ ቡድን በዘጠና ደቂቃ 0 ለ 0 የተለያዩ ሲሆኑ በተሰጠ የመለያ ምት አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ 5 ለ 3 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፍሬ ይህ አይነቱ የስፖርት ውድድር ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀው የዋንጫ ባለቤት ለሆነው የዙሪያ ወረዳው እግር ኳስ ቡድን ለማበረታቻ የሚሆን የ200ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ እግር ኳስ ቡድን አንበል ነብዩ ናሳ የዋንጫ አሸናፊ በመሆናቸው መደሰቱን ገልፆ አሸናፊ መሆን የቻልነው ከ3 ወር በፊት ቀድመን መዘጋጀት በመቻላችን ነው ብሏል።

የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀኔ በበኩላቸው ውድድሩ የዞኑን ማህበረሰብ በማቀራረብ አኳያ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ዞኑን  በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የሚወክሉ ምርጥ ስፖርተኞን ከማፍራት አኳያ ስኬታማ የሆነ ውድድር እንደነበር አመላክተዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ እንደገለፁት፤ ዞኑ በሸማ ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስም ጥበብን ያሳየ ነው።

እንዲሁም በሌሎችም የስፖርት ዓይነቶችና በባህል ስፖርት ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በዕለቱም 150 የሚሆኑ መክፈል የማይችሉ ተማሪዎችን በነፃ በዲግሪ እያሰተማረ ያለው ፖርክ ላንድ ኮሌጅ ዞኑን በመወከል በእግር ኳስ ለሚሳተፈው ቡድን የሚሆን መለያ ከ25ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግና በመግዛት ለዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስረክቧል።

በመጨረሻም ኮከብ አሰልጣኞችና ዳኞች እንዲሁም ጎል አግቢዎች በተጨማሪም በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ኮከብ ተጨዋቾችና ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ቡድኖች የዋንጫ የምስክር ወረቀትና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ እግር ኳስ ቡድን ዋንጫ ከፍ ያደረገ ሲሆን የተለያዩ ትርዒቶች ዕለቱን አድምቀውታል።

ዘጋቢ፡ ታምሩ በልሁ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን