ባለፉት 6 ወራት ከ20 ሺህ በላይ ጎብኝዎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል – የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጎብኝዎች ባለፉት 6 ወራት በጌዴኦ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውን የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም ከተለያዩ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመሆን የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት መሰራት በሚገባቸው ሰፊ ስራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
ባለፉት 6 ወራት ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው መጥተው ጎብኝተዋል ያሉት የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ጂሎ ከአፈፃጸም አንጻር ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የጌዴኦ ባህላዊ መልክአ ምድር በዓለም ቅርስነት ከመመዝገቡ ባሻገር ለጉብኝት ክፍት በማድረግ ዙሪያ ወጣቶች ቦታዎችን በማስጎብኘት በርካታ ስራዎች መሰርታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 10 ሺህ ትክል ድንጋዮች ውስጥ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑት ጌዴኦ ውስጥ እንደሚገኙ በመጥቀስ ቅርሶችን ከማስተዋወቅ አንፃር በክረምቱ ወራት ከተሰሩ ከፍተኛ ስራዎች መካከል ዋነኛው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ባህል እሴቶችን ከማስተዋወቅ ረገድም ባለፈው የካቲት ወር የተከበረው የ2016 ዓ.ም የጌዴኦ ዘመን መለወጫ ደራሮ በዓል ወቅት መምሪያው በዓሉን ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ጭምር እንዲያውቁት ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ መስራቱን አክለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የ20 ሺህ ሲኒ እና 21 ሜትር ደራሮ ቀርቦ በአፍሪካ ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ መስፈር መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው አፈጻጸም ከ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የማስተዋወቁ ስራ አመርቂ መሆኑን አቶ ደርቤ ገልፀዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ህዝብ በታታሪነቱ ብሎም በዛፍ፣ በቡና እና እንሰት ይታወቃል ያሉት አቶ ደርቤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ጭምር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ሌሎችም የጌዴኦ የቱሪስት መዳረሻዎችን በመጎብኘት ኢንቨስት በማድረግ አንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል የመምሪያ ኃላፊው፡፡
ዘጋቢ፡ ቤተልሔም ለገሰ
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ