በቴክኖሎጂ ረገድ ያሉ ድክመቶችና ውስንነቶችን በማረም ለህዝብ ጥቅም መሥራት ይገባል

በቴክኖሎጂ ረገድ ያሉ ድክመቶችና ውስንነቶችን በማረም ለህዝብ ጥቅም መሥራት ይገባል

ሀዋሳ፡ መጋቢት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቴክኖሎጂ ረገድ ያሉብንን ድክመቶችና ውስንነቶች በማረምና የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደማገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የድጋፍና ክትትል ግብረ መልስ እና በቀጣይስራዎች ዙርያ በአርባምንጭ ከተማ ሲያካሂድ የነበረው የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተካልኝ ጋሎ ከኢኮቴ አኳያ እየተሰራ ያለው የስልጠናም ሆነ የጥገና ስራ የሚበረታታ ቢሆንም በቴክኖሎጂ ረገድ ለክልላችን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት አለብን ብለዋል።

የተቋሙ ዋነኛ ትኩረት የተለያዩ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ዘርፍ መደገፍና መከታተል በመሆኑ ያለንን አቅም በማሳደግ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታረቀኝ በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችን ተሞክሮ ማገዝ ይገባልም ብለዋል።

በሆስፒታሎች የጨረራ መሳርያዎችን መፈተሽና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ከመስራት ባሻገር ከዩኒቨርስቲዎችና ከፖሊ ቴክኒክ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂውን በተገቢው መጠቀም ማፍለቅና ማጠናከር እንዲሁም የነበሩ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን በመለየትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቀሪ ወራት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊና የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራ ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጳውሎስ በበኩላቸው እንደ ሀገር ከሳይንስ ዘርፍ አንጻር ትልቅ አቅም ያለው ክልል በመሆኑ ከፈጠራ ስራዎች አንጻር ያሉ ጅምሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

በትምህርት ቤቶችን የሳይንስ ክበባትን በማጠናከር ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ የተሳካ ስራ እንዲሰሩ ወጣቶችን መደገፍና ኤግዚቢሽኖች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የፈጠራ ስራዎች በአእምሮዊ ንብረት እንዲመዘገብ በዘርፉ ሰፊ ስራ ያስፈልጋልም ብለዋል አቶ ዘላለም።

የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማስፋፋትና ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የክልሉ ህዝብ ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባልና የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይነህ ባህሩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባና የሪፎርም ስራዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ከፈጠራ ስራዎች ጋር ተያይዞ ቢሮው እያደረገ ያለውን ድጋፍና እገዛ በማጠናከር በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሀገርን የሚያስጠሩ ወጣቶችን ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ- ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን