የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር ተነጋግሮና ተወያይቶ እየሠራ ይገኛል –  ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ

የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር ተነጋግሮና ተወያይቶ እየሠራ ይገኛል –  ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ

ሀዋሳ: የካቲት 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ የክልሉ መንግስት ከህዝብ ጋር ተነጋግሮና ተወያይቶ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል::

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን ዱራሜ ዲስትሪክት ከሾኔ- አጀባ – ማዞሪያ ድረስ የተገነባው የ18 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ  ተመርቋል::

በምረቃው  መርሀግብር  የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ የክልሉ መንግስት ከጅምሩ ህዝብን በልማት ጉዳይ ላይ በማወያየትና በማነጋገር  እንዲሁም በማቀድ በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል::

መንገድ ወሳኝ የልማት አንቀሳቃሽ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል::

የክልሉ መንግስት በቀጣይም በርካታ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ  ይሠራል ያሉት ዶ/ር ዲላሞ ከሾኔ – አጀባ – ማዞሪያ ድረስ ያለው መንገድ በመጠናቀቁ ለአካባቢው ማህበረሰብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል::

የተሠራውን መንገድ በአግባቡ መያዝ ከቻልን መንገዱ ለታለመለት አላማ እና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ነው:: በመሆኑም ህብረተሰቡ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል::

በክልሉ የተጀመሩ ብዙዎቹ  የመንገድ ፕሮጀክቶች ብዙ ሀብት የሚጠይቁ ናቸው ያሉት ደግሞ በምክትል  ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑሪዬ  ናቸው::

ብዙ ሀብት የሚጠይቁ  መሆናቸው ደግሞ በጊዜ ለማጠናቀቅ ፈተና ሆኗል:: በቀጣይ ግን በግባታ ሂደት ላይ ያሉትን ለማጠናቀቅ የክልል መንግስት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል::

የሀዲያ  ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ መንገዱ በሀዲያና እና ከምባታ ዞን ለሚኖሩ ዜጎች ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ ፋይዳ  ይኖረዋል ብለዋል::

ዛሬ የተመረቀው እና በ2014 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ከሾኔ- አጀባ – ማዞሪያ ድረስ የተገነባው የ18 ኪ.ሜ የጠጠር መንገድ  18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ  ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የዱራሜ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ኃይሌ አበራ ተናግረዋል::

አጠቃላይ ወጪው በክልሉ መንግስት መሸፈኑንም ነው ያስታወቁት::

በምረቃ መርሀግብር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬን ጨምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑሪዬ እና ሌሎችም የክልል፣ የዞንና  የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች በምልከታው ተገኝተዋል::

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ