ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን የሰላም የመቻቻል እና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ተገኝተዋል – አቶ ጥላሁን ከበደ

ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን የሰላም የመቻቻል እና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ተገኝተዋል – አቶ ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፡ የካቲት 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ስድስት ወራት ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ተገኝቷል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አቶ ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡

በባስኬቶ ዞን ላስካ ከተማ ህዝባዊ ኮንፈረንስ በመካሔድ ላይ ነው።

በዚህ መድረክ የተለያዩ የህብረተሰብ አደረጃጀቶች  እና የህዝብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

በርካታ የመልካም አስተዳደር፣ የፀጥታ ጥበቃ እና የመሠረተ  ልማት ፍትሃዊ ስርጭት፣ የንፅህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በጤና ተቋማት የመድሀኒት እና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ክፍተት  የግብርና ግብዓት ተደራሽነት ድክመት፣ ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ እንዲፈታ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።

በኢንቨስትመንት ስም መሬት በመውሰድ ወደ ስራ አለመግባት፣ በአርብቶ አደር ድንበር አከባቢዎች በሳር ግጦሽ እና በውሃ ምክንያት ግጭት መነሳቱ፣ የማህበረሰብ ሬዲዮ አለመቋቋሙ በአከባቢው ቅሬታ እንደፈጠረ ተሳታፊዎቹ  አንስተዋል።

የባስኬቶ አከባቢ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀገ በመሆኑ ይሄን ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠር በጋራ መስራት ይገባል የሚል ሀሳብ ተነስቷል ።

የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሬው ፍሻለው በበኩላቸዉ  በዞኑ አዋሳኝ አከባቢዎች እየተነሱ ያሉ ግጭቶች የዞኑን ነባራዊ ሁኔታ እየጎዳው በመሆኑ ከክልሉ መንግሥት ጋር ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው ብለዋል።

ዞኑ በውሃ ሀብት እጅግ የበለፀገ ነው ያሉት አቶ ፍሬው፥ በዞኑ ያሉ የወንዝ አማራጮችን በመጠቀም ተጨማሪ የመስኖ የልማት ሥራዎችን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ዋና  ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ ልማቱም ሆነ መልካም አስተዳደሩ እንዲፀና ሰላምን ማስፈን የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ይገባል ነው ያሉት::

በሚፈጠሩ መድረኮች በተደጋጋሚ የሰላም ጉዳይ ከህብረተሰቡ መነሳቱ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለፉት አመታት የታፈኑ የህዝብ አጀንዳዎች  አሁን እየተፈጠሩ ላሉ አለመረጋጋቶች ምክንያትቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ችግሮችን በስክነት መፍታት አለብን ብለዋል።

በወሰን አከባቢዎች የሚፈጠሩ  አለመግባባቶችም ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ ሊፈታ ይገባል::

ችግሮች ሌላ ችግር በሚፈጥሩ መልኩ  ሳይሆን በጋራ በመልማትና በወንድማማችነት መንፈስ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል::

ሀገርን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ለነገ የሚባል ባለመሆኑ መንግሥት ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ይሰራል ብለዋል አቶ አማየሁ ባውዲ::

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፥ የባስኬቶ አከባቢ በተፈጥሮ የበለፀገ የሰጡትን እጥፍ ድርብ አድርጎ የሚሰጥ አከባቢ ስለመሆኑ አንስተው ይሄን መልካም ዕድል አይንን ከፈት አድርጎ መጠቀም ከእኛ የሚጠበቅ ነው ብለዋል።

የባስኬቶ ዞንን ማዕከል ያደረጉ ሀገር አቀፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች በዞኑ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።

ከመንገድ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከሚመመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል ብለው ከወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ማህበረሰብ እራሱ እንዲፈታ አሳስበዋል::

ለማህበረሰብ ሬዲዮ የሚያገለግሉ አብዛኛው ዕቃዎች የመጡ በመሆኑ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ይደረጋል ብለዋል::

የመጠጥ ውሃ ችግርን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተሰራ ስለመሆኑ የተነሳ ሲሆን በግንባታው ወቅት ውስብስብ ችግሮች እንደገጠሙ አቶ ጥላሁን አንስተው ይሄን ችግር በመሻገር ለአገልግሎት እንዲበቃ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

በአርብቶ አደር አዋሳኝ አከባቢዎች የሚፈጠሩ የዘረፋና የግዲያ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚሰሩ ህጋዊና ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው የአከባቢን ህብረተሰብ አኗኗር ዘይቤ መቀየር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ልዩነት ላይ ሳይሆን የጋራ አንድነት ላይ  መስራት ፍቅርና ሰላምን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

በዞኑ ያሉ ፀጋዎችን በመለየት በትብብር እና በአንድነት መንፈስ ለህብረተሰቡ ለውጥ በጋራ እንዲሰራም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል::

ዘጋቢ፡ ጀማል የሱፍ