ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ክልሉ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው – ዶ/ር አብርሃም አለማየሁ

ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ክልሉ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው – ዶ/ር አብርሃም አለማየሁ

ሀዋሳ: የካቲት 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉ ህዝብ ለሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ሲሉ በፌዴራል ፓርላማ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም አለማየሁ ተናግረዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራል ፓርላማ እና የክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት ከወከላቸው ህዝብ ጋር ያደረጉት የውይይት ግብረመልስ ማቅረቢያ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው::

በክልሉ የሚኖሩ 20 ሺ ሰዎች ማወያየት መቻሉን የተናገሩት በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም አለማየሁ በውይይት መድረኩ የተነሱ ሀሳቦችን፣ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎችንና ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል::

ከህዝብ ጋር በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የሠላምና ፀጥታ፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ የፕሮጀክት አፈፃፀም እናየሌብነት፣ ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች መነሳታቸውን አስረድተዋል::

በሠላምና ፀጥታ ረገድ በክልል መንግስት የተከናወነው ተግባር አበረታች መሆኑን ተናግረዋል::

በመስቃንና ማረቆ አካባቢ ሠላም ለማስፈን ከህዝብ ጋር የተሠራው ሥራ ውጤት ማምጣቱን በአብነት አንስተዋል::

በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር የክልሉን ሠላም ለማወክ ሲደረግ የነበረው ጥረት መክሸፉ የክልሉ መንግስት ለክልሉ ህዝብ ሠላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ከህዝብ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ያሳያሉ ብለዋል::

ከኢኮኖሚው አንፃር አምና ይስተዋል የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ዘንድሮ መሻሻሉን ገልፀዋል:: ይህም በአርሶ አደሩ ዘንድ መነቃቃትን መፍጠሩን አስረድተዋል::

የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎችም ውጤት በማምጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል::

በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በክልሉ ከደመወዝ ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮች መቀረፋቸውን አስታውቀዋል::

የመፅሀፍት እጥረት ለመቅረፍ እስከ ቀበሌ ድረስ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን በውይይት መድረኩ መገንዘባቸውንም ነው የተናገሩት::

ከፕሮጀክት አፈፃፀም ጋር ያሉ በርካታ ጥያቄዎች በህዝብ ዘንድ መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የክልሉ መንግስት የሚያከናውናቸው ተግባራት መልካም የሚባል ነው ብለዋል:: በመሆኑም የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ ብለዋል::

ከሌብነትና ብሉሹ አሰራር ጋር ተያይዞ በተለይም የማዳበሪያ እዳ ጉዳይ ህዝብ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያነሳው ነው ያሉት ዶ/ር አብርሃም አሁን ችግሩን ለመፍታት ወረዳዎችና ዞኖች የኦዲት ሥራ መጀመራቸው ጥሩ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል::

በክልሉ የተጀመረው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ሥራ ህዝብ በተደጋጋሚ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል::

በአንፃሩ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ ባለው መንገድ ላይ የሚፈጠር የፀጥታ ስጋት: ምሥራቅ ጉራጌ አካባቢ ሸኔ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ: በወረዳዎችና ከተሞች አካባቢ የንጥቂያ ወንጀል መበራከት: የሆስፒታል ተደራሽነት ችግር: የኑሮ ውድነት እና የሥራ እድል ፈጠራ ሥራ አሁንም ትኩረት የሚሹና የክልሉ ህዝብ ያነሳቸው ነጥቦች መሆናቸው ምክትል ሰብሳቢው አብራርተዋል::

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ