ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በቡታጅራ ከተማ የልማት ሥራዎችን ተመለከቱ

ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በቡታጅራ ከተማ የልማት ሥራዎችን ተመለከቱ

ሀዋሳ: የካቲት 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው የተመራ የክልሉ አመራር በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተመልክቷል::

በርእሰ መስተዳድር እንዳሻው የተመራ የክልሉ አመራር በቡታጅራ ከተማ የኢንቨስትመንትና ግብርና ልማት ሥራዎን ተመልክቷል::

በከተማው 12 ሺ ስኴዌር ሜትር ላይ ያረፈው የደስታ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ  የጉብኝቱ  አካል ነው::

ፋብሪካው ከ1ሺ 400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል:: የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል::

በሌላ በኩል በከተማው ወጣቶች በማህበር ሆነው ችግኝ በማፍላት የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች በማቅረብ የሚሰሩትን ሥራ ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ተመልክተዋል::

በዞኑ የአትክልና ፍራፍሬ እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ሥራ አበረታች መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ተናግረዋል::

ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው በከተማው የተመለከቷቸው የኢንቨስትመንትና የሥራ እድል ፈጠራ ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል::

በልማት ላይ ሳንታክት በመሥራት እራሳችንን ከመቻል አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው::

በመስክ ምልከታው ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ በብልፅግና  ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ በምክል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ ኑሪዬ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል እና ሌሎችም ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች በመስክ ምልከታው ተሳትፈዋል::

ዘማሬ ቃጦ